2 ቆሮንቶስ 6:4-10
2 ቆሮንቶስ 6:4-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን በሁሉ ራሳችንን አቅንተን፥ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንሁን፤ በብዙ ትዕግሥትና በመከራ፥ በችግርና በጭንቀት ሁሉ፥ በመገረፍና በመታሰር፥ በድካምና በመታወክ፥ በመትጋትና በመጾም፥ በንጽሕናና በዕውቀት፥ በምክርና በመታገሥ፥ በቸርነትና በመንፈስ ቅዱስ፥ አድልዎ በሌለበት ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኀይል ለቀኝና ለግራ በሚሆን የጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በምርቃትና በርግማን፥ እንደ አሳቾች ስንታይ እውነተኞች ነን። እንደማይታወቁ ስንታይ የታወቅን ነን፤ እንደ ሰነፎች ስንታይም ልባሞች ነን፤ እንደ ሙታን ስንታይ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆንም አንገደልም። ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን እናበለጽጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ በእጃችን ነው።
2 ቆሮንቶስ 6:4-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣ በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣ በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣ በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ ሐዘንተኞች ስንሆን ሁልጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።
2 ቆሮንቶስ 6:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።
2 ቆሮንቶስ 6:4-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይልቅስ መከራንና ችግርን ጭንቀትንም እየታገሥን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን በማናቸውም መንገድ እናቀርባለን። የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን የምንገልጠውም በመገረፍ፥ በመታሰር፥ በመታወክ፥ በሥራ በመድከም፥ እንቅልፍ በማጣትና በመራብ ነው፤ እንዲሁም በንጽሕና፥ በዕውቀት፥ በትዕግሥት፥ በደግነት፥ በመንፈስ ቅዱስ በመመራትና ግብዝነት በሌለበት ፍቅር፥ በእውነት ቃልና በእግዚአብሔር ኀይል ነው። የማጥቂያም ሆነ የመከላከያ መሣሪያችን ጽድቅ ነው፤ ለክብር ወይም ለውርደት ለመወቀስ ወይም ለመመስገን የተዘጋጀን ነን፤ እውነተኞች ስንሆን፥ አታላዮች ተባልን። የታወቅን ስንሆን፥ እንዳልታወቅን ሆነን፥ ሞተዋል ስንባል፥ ሕያዋን ሆነን እንገኛለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ ሐዘን ቢደርስብንም ዘወትር እንደሰታለን፤ ድኾች ሆነን ሳለ፥ ብዙዎችን ሀብታሞች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን፥ ሁሉ ነገር አለን።
2 ቆሮንቶስ 6:4-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች በሁሉም መንገድ ራሳችንን እንሰጣለን፤ በታላቅ ጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በመታሰር፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመራብ፥ በንጽሕና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእውነተኛ ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝ እጅና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል። አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።