2 ቆሮንቶስ 5:18-21
2 ቆሮንቶስ 5:18-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ከአስታረቀን፥ የማስታረቅ መልእክትንም ከሰጠን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ኀጢአታቸውን ይቅር ብሎ በደላቸውንም ሳያስብ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለሙን ከራሱ ጋር አስታርቆአልና፤ የዕርቅ ቃሉንም በእኛ ላይ አደረገ፤ የይቅርታውንም መልእክት ሰጠን። እኛስ በክርስቶስ አምሳል እንለምናለን፤ እግዚአብሔርም በእኛ መጽናናትን ይሰጣችኋል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኋለን። ኀጢአት የሌለበት እርሱ እኛን ለእግዚአብሔር ያጸድቀን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን እንደ ኃጥእ አድርጓልና።
2 ቆሮንቶስ 5:18-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን። ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።
2 ቆሮንቶስ 5:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።
2 ቆሮንቶስ 5:18-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም ሁሉ የሆነው እኛን ከራሱ ጋር በክርስቶስ አማካይነት ባስታረቀንና የማስታረቅንም አገልግሎት በሰጠን በእግዚአብሔር ነው። ይህም እግዚአብሔር በክርስቶስ የዓለምን ሰዎች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ ማለት ነው፤ በደላቸውንም አልቈጠረባቸውም፤ ለእኛም ሰውን ከጌታ ጋር የምናስታርቅበትን ቃል ሰጠን። እግዚአብሔር ሰዎችን በእኛ አማካይነት ስለሚጠራ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ ስለዚህ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!” ብለን በክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን። እኛ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተካፋዮች እንድንሆን እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበትን ክርስቶስን የእኛን ኃጢአት እንዲሸከም አደረገው።
2 ቆሮንቶስ 5:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል። ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው።