2 ቆሮንቶስ 4:1-18
2 ቆሮንቶስ 4:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ እንደ ቸርነቱ የሰጠን ይህ መልእክት አለንና አንሰለችም። ነገር ግን በስውር የሚሠራውን አሳፋሪ ሥራ እንተወው፤ በተንኰልም አንመላለስ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅል፤ ለሰውም ሁሉ አርአያ ስለ መሆን እውነትን ገልጠን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን እናጽና። ወንጌላችን የተሰወረ ቢሆንም እንኳ፥ የተሰወረባቸው ለሚጠፉት ነው። እግዚአብሔርን የሚመስለው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ ልባቸውን አሳውሮአልና። ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታ እንደ ሆነ እንሰብካለን እንጂ ራሳችንን የምንሰብክ አይደለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ብለን ራሳችንን ለእናንተ አስገዛን። በጨለማ ውስጥ “ብርሃን ይብራ” ያለ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት ብርሃን በልባችን አብርቶልናልና። ነገር ግን ከእኛ ያይደለ ከእግዚአብሔር የተገኘ ታላቅ ኀይል ይሆን ዘንድ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ይህ መዝገብ አለን። በሁሉ መከራን እንቀበላለን፤ ነገር ግን አንጨነቅም፤ እንናቃለን፥ ነገር ግን ተስፋ አንቈርጥም። እንሰደዳለን፤ ነገር ግን አንጣልም፤ እንወድቃለን፤ ነገር ግን አንጠፋም። የክርስቶስ ሕይወቱ በዚህ በሟች ሰውነታችን ላይ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር የክርስቶስን ሞት በሥጋችን እንሸከማለን። በሕይወት የምንኖር እኛም በሟች ሰውነታችን ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር ስለ ኢየሱስ ክስርቶስ ብለን ተላልፈን ለሞት እንሰጣለን። ስለዚህም ሞት በእኛ ላይ፥ ሕይወትም በእናንተ ላይ ይሠራል። አንድ የእምነት መንፈስ አለን፤ መጽሐፍ፥ “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” እንዳለ እኛም አመን፤ ስለዚህም ተናገርን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስነሣው እርሱ እኛንም እንደ እርሱ እንዲያስነሣን፥ ከእናንተም ጋር በፊቱ እንዲያቆመን እናውቃለን። ጸጋው በብዙዎች ላይ ትትረፈረፍ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርም የክብሩ ምስጋና ይበዛ ዘንድ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና። ስለዚህ አንሰልች፤ በውጭ ያለው ሰውነታችን ያረጃልና፤ በውስጥ ያለው ሰውነታችን ግን ዘወትር ይታደሳል። ቀላል የሆነው የጊዜው መከራችን ክብርንና ጌትነትን ለዘለዓለም አብዝቶ ያደርግልናልና። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ተስፋ አናደርግም፤ የሚታየው ኀላፊ ነውና፥ የማይታየው ግን ለዘለዓለም የሚኖር ነው።
2 ቆሮንቶስ 4:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቈርጥም። ነገር ግን ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ አናታልልም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋር አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው። የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሯል። እኛ የምንሰብከው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ መሆኑን እንጂ ራሳችንን አይደለምና፤ እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ አገልጋዮች ሆነናል። በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቷልና። ነገር ግን ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን። ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁልጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና። እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ። “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እኛም በዚያው የእምነት መንፈስ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እኛንም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር አስነሥቶ ከእናንተ ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኗል። ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።
2 ቆሮንቶስ 4:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና። ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል። ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና። ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።
2 ቆሮንቶስ 4:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በምሕረቱ ይህን አገልግሎት ስለ ሰጠን ተስፋ አንቈርጥም። ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደናል፤ በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንለውጥም፤ ይልቅስ እውነትን በይፋ እናሳያለን፤ ራሳችንንም ለሰው ሁሉ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ እናደርጋለን። ያስተማርነው የወንጌል ቃል ምናልባት የተሰወረ ቢሆንም የተሰወረው ለሚጠፉት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው። እኛ የምናስተምረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ የእናንተ አገልጋዮች መሆናችንን ነው እንጂ ስለ ራሳችንስ አንሰብክም። “ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይብራ!” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር በክርስቶስ መልክ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ክብር የማወቅ ብርሃን እንዲሰጠን ብርሃኑን በልባችን ውስጥ እንዲበራ አደረገ። ነገር ግን ይህ ከሁሉ የሚበልጠው ኀይል የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አለመሆኑ እንዲታወቅ ይህን ክቡር ነገር እንደ ሸክላ ዕቃ ሆነን ይዘነዋል። በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፤ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቈርጥም፤ ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፤ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፤ የኢየሱስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሞት በእኛም ሰውነት ላይ ዘወትር ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት በሟች ሰውነታችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋኑ ስለ ኢየሱስ ሁልጊዜ ለሞት ተላልፈን እንሰጣለን። ስለዚህ እኛ መላልሰን ለሞት ስንጋለጥ እናንተ ግን ለሕይወት ትጋለጣላችሁ። ይሁን እንጂ “አመንኩ፤ ስለዚህ ተናገርኩ” ተብሎ እንደ ተጻፈው፥ እኛም ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን። ጌታ ኢየሱስን ከሞት ያስነሣ አምላክ እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሣንና ከእናንተም ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም የሆነው ጸጋ ተትረፍርፎ ለብዙ ሰዎች በደረሰ መጠን ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆነው ምስጋና እንዲበዛ ነው። ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ምንም እንኳ የውጪው ሰውነታችን ቢጠፋ የውስጡ ሰውነታችን በየቀኑ ይታደሳል። ይህም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነ መከራችን ወደር የሌለውን እጅግ ታላቅ የሆነ ዘለዓለማዊ ክብር ያስገኝልናል። እኛ የምንጠብቀው የማይታየውን ነገር እንጂ የሚታየውን አይደለም፤ የሚታየው ነገር ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘለዓለማዊ ነው።
2 ቆሮንቶስ 4:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ይህ አገልግሎት የተሰጠን በእግዚአብሔር ምሕረት ምክንያት ስለሆነ፥ መቼም አንታክትም። የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናል፤ በተንኮል አንመላለስም ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናቀርባለን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። እንደ እነርሱ ከሆነ የማያምኑ ሰዎችን ልቦና፥ የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ አሳውሯል። እኛ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፤ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባርያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት እንዲሰጥ ብርሃን በልባችን ውስጥ ያበራ፥ “በጨለማ ብርሃን ይብራ፤” ያለው እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን ይህ ልዩ ኃይል የእግዚአብሄር መሆኑንና ከእኛ አለመመጣቱን ግልጽ ለማድረግ፥ ይህ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ ከየአቅጣጫው መከራን እንቀበላለን እንጂ አንጨነቅም፤ ግራ እንጋባለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንተውም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን እንዲገለጥ፥ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን እንዲገለጥ፥ እኛ ሕያዋን የሆንን ስለ ኢየሱስ ስንል ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን። ስለዚህ ሞት በእኛ፥ ሕይወት ግን በእናንተ ይሠራል። ነገር ግን “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን። ምክንያቱም ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሣንና ከእናንተም ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ፥ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን እንዲያበዛ፥ ሁሉም ነገር ስለ እናንተ ሆኗል። ስለዚህ አንታክትም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድ እንኳን፥ ውስጣዊው ሰውነታችን በየዕለቱ ይታደሳል። ቀላል የሆነው ጊዜያዊ መከራችን ከመመዘኛዎች ሁሉ ለሚያልፈው ለዘላለማዊ ክብር ያዘጋጀናል። ስለዚህ የሚታየውን ሳይሆን የማይታየውን እንመልከት፥ ምክንያቱም የሚታየው ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።