2 ቆሮንቶስ 3:7-11
2 ቆሮንቶስ 3:7-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚያ ስለ አለፈው የፊቱ ብርሃን የእስራኤል ልጆች የሙሴን ፊት መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ በዚያች በድንጋይ ላይ በፊደል ለተቀረጸች ለሞት መልእክት ክብር ከተደረገላት፥ ለመንፈስ ቅዱስ መልእክትማ ምንኛ እጅግ ክብር ሊደረግ ይገባ ይሆን? ኵነኔን ለምታመጣ መልእክት ብዙ ክብር ከተደረገላት የጽድቅ መልእክትማ ምን ያህል ትከብርና ትመሰገን ይሆን? በዚህ ፍጹም ክብር ባነጻጸሯት ጊዜ የከበረችው እንዳልከበረች ትሆናለችና። ያ የሚያልፈው ክብር ካገኘ፥ ያ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት እጅግ ክብር ያገኝ ይሆን?
2 ቆሮንቶስ 3:7-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እስራኤላውያን ከፊቱ ክብር የተነሣ የሙሴን ፊት ትኵር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ፣ ያ ከጊዜ በኋላ የሚያልፈውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው የሞት አገልግሎት በክብር ከመጣ፣ ታዲያ፣ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ከዚያ የላቀ ክብር አይኖረውም? ሰዎችን የሚኰንነው አገልግሎት የከበረ ከሆነ፣ የሚያጸድቀው አገልግሎት የቱን ያህል ይበልጥ የከበረ ይሆን! ከዚህ በፊት ክቡር የነበረው የላቀ ክብር ካለው ጋር ሲወዳደር ክብር የሌለው ሆኗል። የሚያልፈው ያን ያህል ክብር ከነበረው፣ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም?
2 ቆሮንቶስ 3:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና።
2 ቆሮንቶስ 3:7-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕግ የተቀረጸው በድንጋይ ጽላት በፊደል ነበር፤ ሕግ በተሰጠበትም ጊዜ የነበረው ብርሃን እየተወገደ የሚሄድ ቢሆንም እስራኤላውያን የሙሴን ፊት ትኲር ብለው ሊመለከቱት አልቻሉም፤ እንግዲህ ሞትን ያመጣ ሕግ በእንዲህ ዐይነት ክብር ከተገለጠ ታዲያ፥ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚገኘው አገልግሎት የበለጠ ክብር አይኖረውምን? ሰዎች የተኰነኑበት አገልግሎት ይህን ያኽል ክብር ካለው ሰዎች የሚጸድቁበት አገልግሎትማ እንዴት እጅግ የበለጠ ክብር አይኖረውም? የኋለኛው ክብር እጅግ የላቀ ከመሆኑ የተነሣ ያለፈው ክብር ምንም እንዳልነበረው ይቈጠራል። ያ እየደበዘዘ ይሄድ የነበረው ነገር ይህን ያኽል ክብር ከነበረው፥ ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖረው ነገርማ እንዴት እጅግ የበለጠ ክብር አይኖረውም!
2 ቆሮንቶስ 3:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው፥ ስለ ፊተኛው ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት ያን ያህል ክቡር ከሆነ፥ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ልቆ የከበረ አይሆንም? የኩነኔ አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ ይልቁን የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣል። በእርግጥ ያ ከብሮ የነበረው እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት ክብሩን አጥቶአል። ያ ይሻር የነበረው በክብር ከደረሰ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት ልቆ እጅግ አይከብርም!