2 ቆሮንቶስ 2:9-16
2 ቆሮንቶስ 2:9-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም በሁሉ ትታዘዙኝ እንደ ሆነ፥ ፈቃዳችሁን ዐውቅ ዘንድ ጻፍሁላችሁ። ይቅር የምትሉት ቢኖር፥ እኔም ከእናንተ ጋር ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ያልሁትን በክርስቶስ ፊት ስለ እናንተ ይቅር ብያለሁ። ሰይጣን እንዳያታልለን አሳቡን የምንስተው አይደለምና። ለክርስቶስም ወንጌል ጢሮአዳ በደረስሁ ጊዜ በእግዚአብሔር በሩ ተከፈተልኝ። ወንድሜን ቲቶን ስላላገኘሁት ለሰውነቴ ዕረፍት አላገኘሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ ተለይች ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ድል በመንሣቱ የሚጠብቀን፥ በየሀገሩም ሁሉ የዕውቀቱን መዓዛ በእኛ የሚገልጥ እግዚአብሔር ይመስገን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና። የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፥ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው፤ ነገር ግን ይህ የሚገባው ማነው?
2 ቆሮንቶስ 2:9-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር። እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው። ይህንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የርሱን ዕቅድ አንስተውምና። የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤ ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዐዛ ነን። ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ የሕይወት ሽታ ነን፤ ታዲያ፣ ለዚህ ብቁ የሚሆን ማን ነው?
2 ቆሮንቶስ 2:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር። እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥ በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?
2 ቆሮንቶስ 2:9-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያንንም መልእክት የጻፍኩላችሁ ተፈትናችሁ በሁሉ ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለመረዳት ብዬ ነው። እናንተ ይቅርታ ለምታደርጉለት ሰው እኔም ይቅርታ አደርግለታለሁ፤ ይቅር የምልለት በደል ካለ እኔ በክርስቶስ ፊት ይቅርታ የማደርግለት ስለ እናንተ ብዬ ነው። ይህንንም የማደርገው የሰይጣንን የተንኰል ሥራ ስለምናውቅ ሰይጣን እንዳያታልለን ብዬ ነው። ከዚህ በኋላ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ ጌታ ሰፊ የአገልግሎት በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን ወንድሜን ቲቶን ባለማግኘቴ መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ እዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ሄድኩ። ነገር ግን እኛን ዘወትር በክርስቶስ ድል አድራጊዎች አድርጎ ለሚመራንና መልካም መዓዛ እንዳለው ሽቶ ስለ ክርስቶስ ያለንን ዕውቀት በየስፍራው ሁሉ እንድናዳርስ ለሚያደርገን አምላክ ምስጋና ይሁን! እኛ ለሚድኑትም ሆነ ለሚጠፉት መልካም ሽታ እንዳለው ዕጣን በክርስቶስ ለእግዚአብሔር የቀረብን ነን። ለአንዱ የሚገድል የሞት ሽታ ነን፤ ለሌላው ሕይወትን የሚሰጥ የሕይወት መዓዛ ነን፤ ታዲያ፥ ለዚህ አገልግሎት ብቁ የሚሆን ማን ነው?
2 ቆሮንቶስ 2:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን ለማወቅ በማሰብ፥ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበር። እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፤ ይህን የምናደርገው በሰይጣን መበለጥ እንዳንችል ነው፤ ማናችንም የእርሱን አሳብ አንስተውም። የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ በጌታ በሩ ተከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንፈሴ ማረፍ አልቻለም፤ ምክንያቱም እዚያ ወንድሜን ቲቶን አላገኘሁትም። ስለዚህ ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን፥ በእኛም በሁሉም ስፍራ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፥ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?