2 ቆሮንቶስ 2:1-17
2 ቆሮንቶስ 2:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ እያዘንሁ ወደ እናንተ እንዳልመጣ በልቤ ይህን ወሰንሁ። እኔ ካሳዘንኋችሁማ እኔ ካሳዘንሁት በቀር ማን ደስ ያሰኘኛል? የእኔ ደስታ የሁላችሁ እንደ ሆነ በሁላችሁ አምኛለሁና በመጣሁ ጊዜ ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸው ኀዘን እንዳያገኘኝ ይህን ጻፍሁላችሁ። ከብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት የተነሣ በብዙ እንባ ይህን ጽፌላችኋለሁ፤ ነገር ግን እጅግ እንደምወዳችሁ እንድታውቁ ነው እንጂ እንድታዝኑ አይደለም። ማንም ያሳዘነኝ ቢሆን፥ እኔን ብቻ ያሳዘነ አይደለም። ከእናንተ አንድ ሳይቀር ሁላችሁንም አሳዘነ እንጂ፤ አሁንም ሥርዐት አላጸናባችሁም። እንደዚህ ላለው ሰው ከእናንተ ከብዙዎች ያገኘችው ይህች ተግሣጽ ትበቃዋለች። ደግሞም እንዲህ ያለው ሰው ከኀዘን ብዛት የተነሣ እንዳይዋጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል። ስለዚህም ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እማልዳችኋለሁ። ስለዚህም በሁሉ ትታዘዙኝ እንደ ሆነ፥ ፈቃዳችሁን ዐውቅ ዘንድ ጻፍሁላችሁ። ይቅር የምትሉት ቢኖር፥ እኔም ከእናንተ ጋር ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ያልሁትን በክርስቶስ ፊት ስለ እናንተ ይቅር ብያለሁ። ሰይጣን እንዳያታልለን አሳቡን የምንስተው አይደለምና። ለክርስቶስም ወንጌል ጢሮአዳ በደረስሁ ጊዜ በእግዚአብሔር በሩ ተከፈተልኝ። ወንድሜን ቲቶን ስላላገኘሁት ለሰውነቴ ዕረፍት አላገኘሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ ተለይች ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ድል በመንሣቱ የሚጠብቀን፥ በየሀገሩም ሁሉ የዕውቀቱን መዓዛ በእኛ የሚገልጥ እግዚአብሔር ይመስገን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና። የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፥ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው፤ ነገር ግን ይህ የሚገባው ማነው? የእግዚአብሔርን ቃል በሌላ ቀላቅለው እንደሚሸቅጡ እንደ ብዙዎች አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላከ በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ላሳዝናችሁ ስላልፈለግሁ ወደ እናንተ ዳግመኛ ላለመምጣት ወሰንሁ፤ እኔ ባሳዝናችሁም እንኳ፣ ከእናንተው ካሳዘንኋችሁ በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን አለ? ባለፈው ጊዜ እንደዚያ የጻፍሁላችሁ ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ በማለት ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የሁላችሁ ደስታ እንደሚሆን አምናለሁ። እንደዚያ ስጽፍላችሁ በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፣ በብዙም እንባ ውስጥ ነበርሁ፤ ይህንም ያደረግሁት ለእናንተ ያለኝን ጽኑ ፍቅር እንድታውቁ በማለት እንጂ እናንተን ለማሳዘን አልነበረም። ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማግነን አይሁንብኝና፣ ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው። እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው። ደግሞም ከልክ በላይ ዐዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል። ስለዚህ አሁንም የምትወድዱት መሆናችሁን እንድትገልጹለት እለምናችኋለሁ። የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር። እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው። ይህንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የእርሱን ዕቅድ አንስተውምና። የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤ ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዐዛ ነን። ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ የሕይወት ሽታ ነን፤ ታዲያ፣ ለዚህ ብቁ የሚሆን ማን ነው? እኛ እኮ ትርፍ ለማግኘት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ሰዎች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ። እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ፥ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኜአለሁና። በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም። ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር። እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥ በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ እናንተን እንዳላሳዝናችሁ በማሰብ ለጒብኝት ወደ እናንተ ተመልሼ ላለመምጣት ቊርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ምንም እንኳ እናንተን ባሳዝናችሁ ካሳዘንኳችሁ ከእናንተ በስተቀር እኔን የሚያስደስት ማን ነው? እንደዚያ የጻፍኩላችሁም ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ ብዬ ነው፤ የእኔ ደስታ የሁላችሁም ደስታ መሆኑን አምናለሁ። በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፥ በብዙ እንባም ሆኜ የጻፍኩላችሁ በጣም የምወዳችሁ መሆኔን እንድታውቁ ብዬ ነው እንጂ ላሳዝናችሁ ብዬ አይደለም። ሰውን ያሳዘነ ማንም ቢኖር ያሳዘነው እኔን ሳይሆን በደሉን ማጋነን አይሁንብኝ እንጂ በሌላ በኩል ከእናንተ ብዙዎቹን አሳዝኖአል። ለእንዲህ ዐይነቱ ሰው ከእናንተ አብዛኞቹ የፈረዱበት ቅጣት ይበቃዋል። ስለዚህ ይህ ሰው በጣም ከማዘኑ የተነሣ ተስፋ እንዳይቈርጥ ይልቅስ ይቅርታ እንድታደርጉለትና እንድታጽናኑት ይገባል። እንዲሁም እርሱን የምትወዱት መሆናችሁን እንደገና እንድታረጋግጡለት እለምናችኋለሁ። ያንንም መልእክት የጻፍኩላችሁ ተፈትናችሁ በሁሉ ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለመረዳት ብዬ ነው። እናንተ ይቅርታ ለምታደርጉለት ሰው እኔም ይቅርታ አደርግለታለሁ፤ ይቅር የምልለት በደል ካለ እኔ በክርስቶስ ፊት ይቅርታ የማደርግለት ስለ እናንተ ብዬ ነው። ይህንንም የማደርገው የሰይጣንን የተንኰል ሥራ ስለምናውቅ ሰይጣን እንዳያታልለን ብዬ ነው። ከዚህ በኋላ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ ጌታ ሰፊ የአገልግሎት በር ከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን ወንድሜን ቲቶን ባለማግኘቴ መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ እዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ሄድኩ። ነገር ግን እኛን ዘወትር በክርስቶስ ድል አድራጊዎች አድርጎ ለሚመራንና መልካም መዓዛ እንዳለው ሽቶ ስለ ክርስቶስ ያለንን ዕውቀት በየስፍራው ሁሉ እንድናዳርስ ለሚያደርገን አምላክ ምስጋና ይሁን! እኛ ለሚድኑትም ሆነ ለሚጠፉት መልካም ሽታ እንዳለው ዕጣን በክርስቶስ ለእግዚአብሔር የቀረብን ነን። ለአንዱ የሚገድል የሞት ሽታ ነን፤ ለሌላው ሕይወትን የሚሰጥ የሕይወት መዓዛ ነን፤ ታዲያ፥ ለዚህ አገልግሎት ብቁ የሚሆን ማን ነው? እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ንግድ ዕቃ እንደሚቸረችሩት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ቅን መልእክተኞች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን።
2 ቆሮንቶስ 2:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ ዳግመኛ በጉብኝቴ እንዳላስቸግራችሁ ወደ እናንተ ላለመምጣት ቆረጥሁ። እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ስለምተማመን፥ ደስ ሊያሰኙኝ ወደሚገባቸው በመምጣቴ ማስቸገር እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍኩላችሁ። በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት፥ በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበር፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም። ነገር ግን ማንም ያሳዘነ ቢኖር፥ እኔን ብቻ ሳይሆን ያሳዘነው፥ ባላጋንነው በተወሰነ መልኩ፥ ሁላችሁንም ነው። እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ በብዙሃኑ ስለተቀጣ በቂው ነው። ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቆርጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅራችሁን መልሳችሁ እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ። በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን ለማወቅ በማሰብ፥ ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበር። እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፤ ይህን የምናደርገው በሰይጣን መበለጥ እንዳንችል ነው፤ ማናችንም የእርሱን አሳብ አንስተውም። የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ በጌታ በሩ ተከፍቶልኝ ነበር፤ ነገር ግን መንፈሴ ማረፍ አልቻለም፤ ምክንያቱም እዚያ ወንድሜን ቲቶን አላገኘሁትም። ስለዚህ ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን፥ በእኛም በሁሉም ስፍራ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ፥ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚነግዱ እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።