2 ቆሮንቶስ 12:1-6
2 ቆሮንቶስ 12:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ መመካት ይቻለኛል፤ ነገር ግን አይጠቅምም፤ ደግሞም ወደ ጌታ ራእይና መገለጥ እሄዳለሁ። በክርስቶስ ያመነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ዘመኑ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ያን ሰው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ነጥቀው ወሰዱት። ያን ሰው አውቀዋለሁ፤ በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ እግዚአብሔር ያውቃል። ወደ ገነትም ነጥቀው ወሰዱት፤ በዚያም ሰው ሊናገረው የማይችለውን የማይተረጐም ነገር ሰማ። ስለዚህም እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ በመከራዬ እንጂ በራሴስ አልመካም። ልመካ ብሻም አላዋቂ አይደለሁም፤ እውነቱን እናገራለሁና፤ ነገር ግን ስላዩኝና ስለ ሰሙኝ እንደምበልጥ አድርገው እንዳይጠራጠሩኝ ትቸዋለሁ።
2 ቆሮንቶስ 12:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፣ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ። ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል። ይህ ሰው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል፤ እርሱም ወደ ገነት እንደ ተነጠቀ፣ በዚያም በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችል፣ ሰውም እንዲናገረው ያልተፈቀደለት ነገር ሰማ። እንደዚህ ስላለው ሰው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ከደካማነቴ በስተቀር አልመካም። መመካት ብፈልግ እንኳ እንደ ሞኝ መቈጠር የለብኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው። ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው በላይ እንዳይገምተኝ ከመመካት እቈጠባለሁ።
2 ቆሮንቶስ 12:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።
2 ቆሮንቶስ 12:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ምንም እንኳ በመመካት ጥቅም ባይገኝበት መመካት ካስፈለገ ጌታ በሰጠኝ መገለጥና ራእይ እመካለሁ። የክርስቶስ የሆነ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ ይህ ሰው ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ተወሰደ፤ (የተወሰደውም ከነሥጋው ይሁን ወይም አይሁን አላውቅም፤ እግዚአብሔር ያውቃል።) ነገር ግን ይህ ሰው ወደ ገነት እንደ ተወሰደ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ከነሥጋው ይሁን ወይም አይሁን አላውቅም፤ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እርሱ ወደ ገነት ተነጥቆ በሰው ቃል ሊገለጥና ሰውም ሊናገረው የማይችለውን ነገር ሰማ። እንደዚህ ባለው ሰው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ከደካማነቴ በቀር ሌላ የምመካበት ነገር የለም። ታዲያ፥ እኔ እውነት ስለምናገር መመካት ብፈልግም ሞኝ አልሆንም፤ ነገር ግን ማንም በእኔ ላይ ከሚያየውና ከእኔ ከሚሰማው በላይ ግምት እንዳይሰጥ ብዬ ከመመካት እቈጠባለሁ።
2 ቆሮንቶስ 12:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፥ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ። ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት፥ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ እስከ ሦስተኛ ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው አውቃለሁ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ ወደ ገነት ተነጠቀ፤ በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችለውን፥ ሰውም ሊናገር ያልተፈቀደለትን ነገር ሰማ። እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ደካማ ከመሆኔ ሌላ የምመካበት የለኝም። ልመካ ብፈልግ አልሞኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው፤ ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው ባለፈ የበለጥኩ አድርጎ እንዳያስበኝ ይህን ከመናገር እቆጠባለሁ።