1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ፥ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ መልካምን እንዲያደርጉ፤ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፤ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው። ደግሞም መልካም ሥራ እንዲሠሩ፥ በመልካም ሥራ ሀብታሞች እንዲሆኑ፥ ለመለገሥና ያላቸውንም ለማካፈል ዝግጁዎች እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛውን ሕይወት ለማግኘት መሠረቱ ጽኑ የሆነውን ሀብት በሚመጣው ዘመን ለራሳቸው ያከማቻሉ።
1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ በሚያልፍም ባለጠግነት ላይ ሳይሆን እንድንደሰትበት ሁሉን አትረፍርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር ላይ ተስፋ እንዲያደርጉ እዘዛቸው። መልካምን ያድርጉ፥ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች በመሆን ለመለገስና ለማካፈል የተዘጋጁ ይሁኑ፤ በዚህ ዓይነት እውነተኛውን ሕይወት እንዲይዙ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ ያከማቻሉ።