1 ጢሞቴዎስ 5:1-8
1 ጢሞቴዎስ 5:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፤ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው። በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፤ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
1 ጢሞቴዎስ 5:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂ በኀይለ ቃል አትናገረው። ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች ተቀበላቸው፤ እንዲሁም አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና አስተናግዳቸው። በርግጥ ችግረኛ የሆኑትን መበለቶች ተንከባከባቸው። አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና። በርግጥ መበለት የሆነች፣ ብቻዋንም የምትኖር ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ለጸሎትና የእግዚአብሔርን ርዳታ ለመለመን ሌሊትና ቀን ትተጋለች። ምድራዊ ደስታን የምትሻዋ መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት። ማንም የሚነቀፍበት ነገር እንዳይኖር፣ ይህንም ትእዛዝ ለሕዝቡ ስጥ። አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።
1 ጢሞቴዎስ 5:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው። በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
1 ጢሞቴዎስ 5:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሽማግሌን እንደ አባት አድርገህ ምከረው እንጂ አትገሥጸው፤ ወጣቶች ወንዶችን እንደ ወንድሞች፥ አሮጊቶችን እንደ እናቶች አድርገህ ተመልከታቸው፤ እንዲሁም ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከታቸው። በእርግጥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች አክብራቸው። ማንኛይቱም ባል የሞተባት ሴት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት እነዚህ ልጆች አስቀድመው ለቤተሰቦቻቸው የመጠንቀቅን፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው ብድር የመመለስን መንፈሳዊ ግዴታ ይማሩ፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። በእርግጥ መበለት የሆነችና ብቻዋን የምትኖር፥ ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋ ሌሊትና ቀን የእግዚአብሔርን ርዳታ በመለመን በጸሎት ጸንታ ትኖራለች። የዚህን ዓለም ደስታ ብቻ የምትወድ መበለት ግን በቁሟ የሞተች ናት። ያለ ነቀፋ እንዲኖሩም እነዚህን ትምህርቶች ስጣቸው። ለራሱ ዘመዶች፥ ይልቁንም ለቅርብ ቤተሰቦቹ የማያስብ ሃይማኖቱን የካደ ነው፤ እንዲያውም ከማያምን ሰው እንኳ የባሰ ክፉ ነው።
1 ጢሞቴዎስ 5:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሽማግሌን እንደ አባት አድርገህ ምከር እንጂ አትገሥጽ፤ እንዲሁም ጎልማሶችን እንደ ወንድሞች፥ አሮጊቶችን እንደ እናቶች፥ ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከት። በእርግጥ ረዳት የሌላቸውን መበለታትን ተንከባከብ። ማንም መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰቦቻቸው የሃይማኖታዊ ግዴታቸውን መፈጸምን ይማሩ፥ ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ ነውና። በእርግጥ መበለት የሆነችና ያለረዳት ለብቻዋ የተተወች፥ ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ለዚህ ዓለም ደስታ የምትኖር መበለት ግን በሕይወትዋ ሳለች እንኳ የሞተች ናት። ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ እነዚህን ነገሮች ደግሞ እዘዝ። ማንም ቢሆን ግን ለገዛ ዘመዶቹ በተለይም ለቤተ ሰቡ አባላት የማያስብ ከሆነ፥ እምነትን የካደና ከማያምን ሰው ይልቅ የባሰ ነው።