1 ተሰሎንቄ 2:4-8
1 ተሰሎንቄ 2:4-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፤ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፤ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።
1 ተሰሎንቄ 2:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ብለን አይደለም። የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንባችሁ ነበር፤ ነገር ግን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን። የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ።
1 ተሰሎንቄ 2:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። እንደምታውቁ፥ እያቍኦላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጕኦምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።
1 ተሰሎንቄ 2:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይልቅስ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለእኛ በዐደራ የሰጠን በእኛ ተማምኖ ስለ ሆነ እንናገራለን፤ ይህንንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን ነው እንጂ ሰውን ለማስደሰት ብለን አይደለም። አንድም ጊዜ በቃላት በማቈላመጥ ወይም የገንዘብ ፍላጎት ኖሮን ከቶ እንዳልተናገርን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክራችን ነው። ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም ሰው ክብርን አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን አስፈላጊውን ከእናንተ ለመጠየቅ እንችል ነበር፤ ነገር ግን ለልጆችዋ እንደምትጠነቀቅ እናት በገርነት በመካከላችሁ ተመላለስን። እንዲሁም በጣም ስለምንወዳችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ማብሠር ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም እንኳ ልንሰጣችሁ ዝግጁዎች ነበርን።
1 ተሰሎንቄ 2:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው።