1 ሳሙኤል 3:10-18
1 ሳሙኤል 3:10-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፤ እንደ ቀድሞውም ጠራው። ሳሙኤልም፥ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፥ “እነሆ የሰማውን ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ ነገሬን በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ። በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ ላይ አጸናለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ። ልጆቹ በእግዚአብሔር ላይ ክፉ እንዳደረጉ ዐውቆ አልገሠጻቸውምና ስለ ልጆቹ ኀጢአት ለዘለዓለም ቤቱን እንደምበቀል አስታውቄዋለሁ። ስለዚህም የዔሊ ቤት ኀጢአት በዕጣንና በመሥዋዕት ለዘለዓለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።” ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ። ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ፥ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥” አለ፤ እርሱም፥ “እነሆኝ” አለ። እርሱም፥ “እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድን ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህና ከሰማኸው ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፤ እንዲህም ይጨምርብህ” አለው። ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፤ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም፥ “እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ።
1 ሳሙኤል 3:10-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ሁሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ። በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተ ሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ። ዔሊ በሚያውቀው ኀጢአት ምክንያት በቤተ ሰቡ ላይ ለዘላለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር፤ ልጆቹ አስጸያፊ ነገር አድርገዋል፤ እርሱ ግን አልከለከላቸውም። ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቍርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።” ሳሙኤል እስኪነጋ ድረስ ተኛ፤ ከዚያም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ፤ ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ፤ ዔሊ ግን ሳሙኤልን፣ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም፣ “እነሆኝ” ሲል መለሰ። ዔሊም፣ “እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድን ነው? አትደብቀኝ፤ ከነገረህ ውስጥ አንዲቱን እንኳ ብትደብቀኝ እግዚአብሔር እንደዚያው ያድርግብህ፤ ከዚያ ለከፋም ይዳርግህ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ምንም ነገር ሳይደብቅ ሁሉንም ነገረው። ዔሊም፣ “እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ።
1 ሳሙኤል 3:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም፦ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፦ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ። በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፥ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ። ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤቱ ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ። ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ። ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ። ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ፦ ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፥ እርሱም፦ እነሆኝ አለ። እርሱም፦ እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፥ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኽኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው። ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም፦ እርሱ እግዚአብሔር ነው፥ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።
1 ሳሙኤል 3:10-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ከዚያም በፊት ያደርግ በነበረው ዐይነት “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ እሰማለሁና ተናገር” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለው፦ “እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ አንድ ነገር የማደርግበት ቀን ተቃርቦአል፤ ያን ነገር በጆሮው የሚሰማው ሁሉ ይዘገንነዋል። በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ በዔሊና በቤተሰቡ ላይ አስቀድሜ የተናገርኩትን ብርቱ የማስጠንቀቂያ ቃል ሁሉ በተግባር እፈጽማለሁ፤ ልጆቹ በእኔ ላይ የንቀት ተግባር ሲፈጽሙ እርሱ ስላልገሠጻቸው ቤተሰቡን ለዘለዓለም እቀጣለሁ ብዬ ነግሬዋለሁ። ስለዚህ የዔሊ ቤተሰብ ኃጢአት በመሥዋዕትም ሆነ በቊርባን ለዘለዓለም አይሰረይም ብዬ በመሐላ ተናግሬአለሁ።” ሳሙኤልም እስኪነጋ ድረስ ተኝቶ ቈየ፤ በነጋም ጊዜ ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ፤ ያየውንም ራእይ ለዔሊ ለመንገር ፈራ፤ ዔሊ ግን ሳሙኤልን “ልጄ ሳሙኤል ሆይ!” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም “እነሆ አለሁ ጌታዬ!” ሲል መለሰ። ዔሊም “እግዚአብሔር የነገረህ ቃል ምንድን ነው? ከእኔ ምንም ነገር አትደብቅ፤ አንዳች ነገር ብትደብቅ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ብርቱ ቅጣት ያምጣብህ” አለው። ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ሁሉንም ነገር ለዔሊ አስረዳው፤ ሰውሮ ያስቀረው ምንም ነገር አልነበረም፤ ዔሊም “እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግ” አለ።
1 ሳሙኤል 3:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፥ “አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” አለ። ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ጆሮ ሁሉ ዝግንን የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ። በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ። ልጆቹ አስጸያፊ ነገር ሲያደርጉ እርሱ ባለመከልከሉ፥ ዔሊ በሚያውቀው ኃጢአት ምክንያት በቤተሰቡ ላይ ለዘለዓለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር። ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቁርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።” ሳሙኤል እስኪ ነጋ ድረስ ተኛ፤ ከዚያም ተነሥቶ የጌታን ቤት በሮች ከፈተ፤ ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ፤ ዔሊ ግን ሳሙኤልን፥ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም፥ “እነሆኝ” ሲል መለሰ። ዔሊም፥ “እርሱ የነገረህ ነገር ምንድነው? አትደብቀኝ፤ ከነገረህ ውስጥ አንዲቱን እንኳ ብትደብቀኝ እግዚአብሔር እንደዚያው ያድርግብህ፤ ከዚያ የከፋም ያምጣብህ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ምንም ነገር ሳይደብቅ ሁሉንም ነገረው። ዔሊም፥ “እርሱ ጌታ ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ።