1 ሳሙኤል 2:12-21

1 ሳሙኤል 2:12-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የካ​ህ​ኑም የዔሊ ልጆች ክፉ​ዎች ነበሩ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አያ​ው​ቁም ነበር። መሥ​ዋ​ዕት በሚ​ሠዉ በሕ​ዝቡ ሁሉ ዘንድ የነ​በረ የካ​ህ​ኑ​ንም ሕግ አያ​ው​ቁም ነበረ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ መሥ​ዋ​ዕት በሠዉ ጊዜ የካ​ህኑ ብላ​ቴና ይመጣ ነበር፤ በእ​ጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበር፤ ወደ ድስ​ቱም ወይም ወደ ምን​ቸቱ ወይም ወደ አፍ​ላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰ​ድ​ደው ነበር። ሜን​ጦ​ውም ያወ​ጣ​ውን ሁሉ ካህኑ ለእ​ርሱ ይወ​ስ​ደው ነበር፤ በሴ​ሎም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሊሠዉ በሚ​ወጡ በእ​ስ​ራ​ኤ​ላ​ው​ያን ሁሉ ላይ እን​ዲህ ያደ​ርጉ ነበር። ደግ​ሞም ስቡ ሳይ​ጤስ የካ​ህኑ ልጅ መጥቶ የሚ​ሠ​ዋ​ውን ሰው፥ “ጥሬ​ውን እንጂ የተ​ቀ​ቀ​ለ​ውን ሥጋ ከአ​ንተ አይ​ወ​ስ​ድ​ምና እጠ​ብ​ስ​ለት ዘንድ ለካ​ህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። የሚ​ሠ​ዋ​ውም ሰው፥ “አስ​ቀ​ድሞ እንደ ሕጉ ስቡ ይጢስ፤ ኋላም ሰው​ነ​ት​ህን ደስ የሚ​ያ​ሰ​ኛ​ትን ትወ​ስ​ዳ​ለህ” ቢለው፥ እርሱ፥ “አይ​ሆ​ንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ ካል​ሆ​ነም በግድ አወ​ስ​ደ​ዋ​ለሁ” ይለው ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቍር​ባን ይንቁ ነበ​ርና የዔሊ ልጆች ኀጢ​አት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበ​ረች። ሳሙ​ኤል ግን ገና ብላ​ቴና ሳለ የበ​ፍታ ኤፉድ ታጥቆ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ያገ​ለ​ግል ነበር። እና​ቱም ታናሽ መደ​ረ​ቢያ ሠራ​ች​ለት፤ በየዓ​መ​ቱም መሥ​ዋ​ዕት ለመ​ሠ​ዋት ከባ​ልዋ ጋር ስት​ወጣ ትወ​ስ​ድ​ለት ነበር። ዔሊም ሕል​ቃ​ና​ንና ሚስ​ቱን ባረ​ካ​ቸው፥ “ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ አገ​ባ​ኸው ስጦታ ፈንታ ከዚ​ህች ሴት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘር ይስ​ጥህ” አለው፤ እነ​ር​ሱም ወደ ቤታ​ቸው ገቡ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሐናን ጐበኘ፤ ዳግ​መ​ኛም ፀነ​ሰች፥ ሦስት ወን​ዶ​ችና ሁለት ሴቶች ልጆ​ችን ወለ​ደች። ብላ​ቴ​ናው ሳሙ​ኤ​ልም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት አደገ።

1 ሳሙኤል 2:12-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የዔሊ ልጆች ምናምንቴ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር። በዚያ ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋራ ባላቸው ግንኙነት የሚፈጽሙት ወግ ነበር፤ ይኸውም ማንም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይመጣል፤ ወደ ድስቱ ወይም ወደ ቶፋው ወይም ወደ አፍላሉ፣ ወይም ወደ ምንቸቱ ይሰደዋል። ከዚያም ካህኑ ሜንጦው ያወጣውን ማንኛውንም ሥጋ ለራሱ ይወስደዋል። ወደ ሴሎ የሚመጡትን እስራኤላውያን ሁሉ የሚያስተናግዱት በዚህ ዐይነት ነበር። ነገር ግን ሥቡ ገና ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው፣ “ካህኑ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ ስለማይቀበል፣ ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ አለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር። ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ። ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ከባሏ ጋራ ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር። ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን ዐሰባት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

1 ሳሙኤል 2:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፥ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር። ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር። ሰውዮውም፦ አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ፦ አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፥ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር። ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቁርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች። ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፋድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፥ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

1 ሳሙኤል 2:12-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የዔሊ ልጆች ምንም የማይረቡ ስድ አደጎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያከብሩም ነበር፤ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደዚህ ነበር፦ ሰው ሁሉ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው በመብሰል ላይ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይቀርብ ነበር። እርሱም ሜንጦውን ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦው የሚያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር፤ ይህንንም ድርጊት ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በቀር ጮማው ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መሥዋዕቱን ወደሚሠዋው ሰው መጥቶ “ካህኑ ያንተን የተቀቀለ ሥጋ ሳይሆን ጥሬ ሥጋ ስለሚፈልግ ለእርሱ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉትና ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ትወስዳለህ” ቢለው፥ የካህኑ አገልጋይ “አይሆንም! አሁኑኑ ስጠኝ! እምቢ ብትል ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዐይነት የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ስላቃለሉ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና በልጅነቱ ከበፍታ የተሠራ ሸሚዝ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፤ ይህም ቃል በዕብራይስጡ ካህኑ ለሚለብሰው ልብስ ወይም በደረቱ ላይ ስለሚያደርገው ነገር መጠሪያ ነው። እናቱም በየዓመቱ ባልዋን ተከትላ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናን ከሚስቱ ከሐና ጋር በሚመርቅበት ጊዜ፥ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጋችሁ በሰጣችሁት በዚህ ልጅ ፈንታ ከዚህቹ ሴት ሌሎችን ልጆች ይስጥህ!” ይለው ነበር። ከዚያን በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን አስታወሳትና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ ወጣቱ ሳሙኤልም እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ።

1 ሳሙኤል 2:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የዔሊም ልጆች ለጌታ ክብር የማይሰጡ ስድ አደጎች ነበሩ። የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ አገልጋይ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ይህንንም ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ ያደርጉ ነበር። ከዚህም ሌላ፥ ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ አገልጋይ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ “ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም፦ “አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት፥ ከዚያም በኋላ ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ያህል ትወስዳለህ” ቢለው፥ እርሱ፦ “አይሆንም፥ አሁን ልትሰጠኝ ይገባል፤ ካልሆነ ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዓይነት የጌታን መሥዋዕት ስላቃለሉ፥ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በጌታ ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በጌታ ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም በየዓመቱ ከባሏ ጋር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ “ለጌታ ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት ጌታ ዘር ይስጥህ” ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። ጌታም ሐናን አሰበ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በጌታ ፊት አደገ።