1 ሳሙኤል 19:1-7
1 ሳሙኤል 19:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለብላቴኖቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር። ዮናታንም፥ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፤ በስውርም ተቀመጥ። እኔም እወጣለሁ፤ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም ለአባቴ እነግረዋለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ እንዲህም አለው፥ “እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊዉን ገደለ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ታላቅ መድኀኒት አደረገ፤ እስራኤልም ሁሉ አይተው ደስ አላቸው፤ በከንቱ ዳዊትን ትገድለው ዘንድ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ?” ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፤ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።
1 ሳሙኤል 19:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር፣ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጧት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ።
1 ሳሙኤል 19:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፥ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፥ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፥ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፥ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ አንተም አይተህ ደስ አለህ፥ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለ ምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ። ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፥ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፥ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።
1 ሳሙኤል 19:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ማቀዱን ለልጁ ለዮናታንና ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ነገረ፤ ነገር ግን ዮናታን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። በእርሱ ላይ የታቀደውን ነገር ሁሉ እንዲህ ሲል ነገረው፥ “አባቴ ሊገድልህ ዐቅዶአል፤ ስለዚህ እባክህ በነገው ማለዳ ይህ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ፤ ስውር በሆነ ቦታ ተሸሽገህ ቈይ፤ አንተም ተደብቀህ ባለህበት እርሻ ወደ አባቴ ቀርቤ ስለ አንተ አነጋግረዋለሁ፤ የማገኘውንም መልስ እንድታውቀው አደርጋለሁ።” ዮናታንም ዳዊትን በማመስገን ለሳኦል እንዲህ ሲል ነገረው፤ “በአገልጋይህ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አታድርግ፤ እርሱ ምንም ነገር አልበደለህም፤ ይልቅስ እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ታላቅ ጥቅም በማስገኘት ረድቶሃል፤ እርሱ ለሕይወቱ ሳይሳሳ በመጋፈጥ ጎልያድን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም ይህን ባየህ ጊዜ ደስ ብሎህ ነበር፤ ታዲያ አሁን አንተ በንጹሕ ሰው ላይ በደል ለመሥራት ስለምን ታስባለህ? ምክንያት በሌለውስ ነገር ዳዊትን ለመግደል ስለምን ፈለግኽ?” ሳኦልም ዮናታን የተናገረውን ቃል በመስማት ዳዊትን እንደማይገድለው የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በመማል አረጋገጠ፤ ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ይህን ሁሉ ከነገረው በኋላ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ ዳዊትም ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር በንጉሡ ፊት እንደ ቀድሞው ማገልገሉን ቀጠለ።
1 ሳሙኤል 19:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ።