1 ሳሙኤል 17:48-52
1 ሳሙኤል 17:48-52 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊዉን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። ዳዊትም እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፤ ወነጨፈውም፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩን መታው፤ ድንጋዩም ጥሩሩን ዘልቆ በግንባሩ ተቀረቀረ፤ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፤ ገደለውም፤ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ተነሥተው እልል አሉ፤ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በር ድረስ አሳደዱአቸው። የፍልስጥኤማውያንም በድኖቻቸው እስከ ጌትና እስከ አቃሮን በሮች ድረስ በመንገድ ላይ ወደቁ።
1 ሳሙኤል 17:48-52 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኰረጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጋት መግቢያና እስከ አቃሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሽዓራይም አንሥቶ እስከ ጋት ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወድቆ ነበር።
1 ሳሙኤል 17:48-52 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፥ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፥ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፥ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እልል አሉ፥ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በር ድረስ አሳደዱአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ከሸዓራይም ጀምሮ እስከ ጌትና እስከ አቃሮን ድረስ በመንገድ ላይ የተመቱት ወደቁ።
1 ሳሙኤል 17:48-52 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፍልስጥኤማዊው አደጋ ሊጥልበት ወደ ዳዊት በቀረበ ጊዜ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ሄደ። እጁንም ወደ ኮረጆው ከቶ አንዲት ድንጋይ በማውጣት በጎልያድ ላይ ወነጨፈ፤ ድንጋዩም ግንባሩን በጥርቆ ወደ ራስ ቅሉ ገባ፤ ጎልያድም በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ። በዚህም ዐይነት ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ጎልያድን መትቶ በመግደል ድል አደረገ! በእጁም ሰይፍ አልነበረም። ወደ እርሱም ሮጦ በመሄድ በላዩ ላይ ቆመ፤ የጎልያድንም ሰይፍ ከሰገባው በመምዘዝ ራሱን ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም የእነርሱ ዝነኛ ተዋጊ ጎልያድ መገደሉን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየፎከሩ እነርሱን በመከተል እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን የቅጽር በሮች ድረስ አሳደዱአቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ሬሳ እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን ድረስ ወደ ሻዕራይም በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ወደቀ።
1 ሳሙኤል 17:48-52 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፥ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ በግምባሩም ምድር ላይ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጋት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓራይም አንሥቶ እስከ ጋትና ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወደቀ።