1 ሳሙኤል 17:41-45
1 ሳሙኤል 17:41-45 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና፥ መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትርና ድንጋይ ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው። ዳዊትም፥ “የለም ከውሻ ትከፋለህ” አለው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “ወደ እኔ ና፤ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣቸዋለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊዉን አለው፥ “አንተ ሰይፍና ጦር፥ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
1 ሳሙኤል 17:41-45 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም፣ “እስኪ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት ጌታ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
1 ሳሙኤል 17:41-45 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
1 ሳሙኤል 17:41-45 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤
1 ሳሙኤል 17:41-45 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ።