1 ሳሙኤል 17:20-31
1 ሳሙኤል 17:20-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፤ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ፥ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። የእስራኤልና የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትም ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር። ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፤ ወደሚዋጉበትም ሮጦ ሄደ፤ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለ ያ አርበኛ ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፤ ቀድሞ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዬውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከፊቱ ሸሹ። የእስራኤልም ሰዎች፥ “ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፤ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል” አሉ። ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው በውኑ ይህ ይደረግለታል? የሕያው አምላክን ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። ሕዝቡም፥ “ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ ኤልያብም በዳዊት ላይ እጅግ ተቈጣ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን?” አለ። ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፤ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፤ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም ወሰደው።
1 ሳሙኤል 17:20-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጕዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው።
1 ሳሙኤል 17:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፥ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበረ። ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፥ ዳዊትም ሰማ። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ። የእስራኤልም ሰዎች፦ ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፥ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፥ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ። ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሕዝቡም፦ ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፥ የኤልያብም ቁጣ በዳዊት ላይ ነድዶ፦ ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኩራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው። ዳዊትም፦ እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ። ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፥ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፥ ወደ እርሱም አስጠራው።
1 ሳሙኤል 17:20-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳዊትም በማግስቱ ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹን ለሌላ እረኛ በመተው እሴይ ባዘዘው መሠረት የተዘጋጀውን ምግብ ይዞ ሄደ፤ እስራኤላውያን ጦርነት ለመግጠም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚደነፉበት ጊዜ ዳዊት ወደ ጦሩ ሰፈር ደረሰ። የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትና የእስራኤላውያን ሠራዊት ቦታ ቦታቸውን ይዘው በጦሩ ግንባር ፊት ለፊት በመተያየት ላይ ነበሩ። ዳዊትም የያዘውን ምግብ ለስንቅ ጠባቂው ትቶ ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ወደ ወንድሞቹ ሄደ፤ ስለ ደኅንነታቸውም ጠየቃቸው። ዳዊትም ከወንድሞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ የጋት ሰው ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር ወደፊት በማምራት በእስራኤላውያን ላይ መፎከሩን ቀጠለ፤ ዳዊትም የእርሱን ድንፋታ ሰማ። እስራኤላውያንም ጎልያድን ባዩ ጊዜ በታላቅ ፍርሀት ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸውም እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ይህ በየቀኑ እስራኤልን ለመፈታተን የሚወጣውን ሰው ታያላችሁን? ንጉሥ ሳኦል እርሱን ለሚገድልለት ሰው ብዙ ሀብት ለመስጠት ቃል ገብቶአል፤ ሴት ልጁንም እንደሚድርለትና የአባቱም ቤተሰብ ከግብር ነጻ እንደሚያደርግለት ተናግሮአል።” ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እስራኤልን ከዚህ አሳፋሪ ውርደት ለሚያድን ሰው ምን ይደረግለታል? ኧረ ለመሆኑ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት የሚፈታተን ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም ጎልያድን ለሚገድል ሰው ምን እንደሚደረግለት ነገሩት። የዳዊት ታላቅ ወንድም ኤሊአብም ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ እርሱም በዳዊት ላይ በጣም ተቈጥቶ “እዚህ ምን ትሠራለህ? በበረሓ ያሉትንስ እነዚያን ጥቂቶች በጎችህን ለማን ተውካቸው? እኔ ትዕቢተኛነትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ! አሁን የመጣኸው እኮ የጦርነቱን ሁኔታ ለመመልከት ነው!” አለው። ዳዊትም “አሁን እኔ ምን አደረግሁ? ለመጠየቅ እንኳ አልችልምን?” ሲል መለሰለት፤ ከዚያም ወደ ሌላው ሰው መለስ ብሎ ያንኑ ጥያቄ አቀረበለት፤ በጠየቀ ቊጥር የሚያገኘው መልስ ተመሳሳይ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ዳዊት የተናገረውን ቃል ሰምተው ስለ ነበር፥ ሄደው ለሳኦል ነገሩት፤ ሳኦልም ልኮ ዳዊትን አስጠራው።
1 ሳሙኤል 17:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፥ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጉዞ ጀመረ። ልክ ሠራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፥ እነሆ፥ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሃት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፥ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፥ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፥ “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፥ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤሊአብ፥ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውካቸው? ዕብሪትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልምን?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፥ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው።