1 ሳሙኤል 16:15-23
1 ሳሙኤል 16:15-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሳኦልም ብላቴኖች፥ “እነሆ፥ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያስጨንቅሃል፤ አገልጋዮችህ በፊትህ ይናገሩ፤ በበገና የሚዘምር ሰውም ለጌታቸው ይፈልጉለት፤ ክፉ መንፈስም በመጣብህ ጊዜ በገናውን ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ፤ እርሱም ያሳርፍሃል” አሉት። ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፥ “እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና ሲመታ የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ ሰውየውም ጠቢብ፥ ተዋጊም ነው፤ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለ። ሳኦልም ወደ እሴይ መልእክተኞችን ልኮ፥ “ከመንጋዎችህ ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለ። እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ፥ አንድም የፍየል ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዊት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፤ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፤ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። ሳኦልም ወደ እሴይ፥ “በዐይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ እባክህ ይቁም፥” ብሎ ላከ። እንዲህም ሆነ፤ ያ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው፥ ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉው መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:15-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።” ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሳኦል፣ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቍማዳ በአህያ አስጭኖ፣ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፣ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። ከዚያም ሳኦል፣ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ። ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፣ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:15-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሳኦልም ባሪያዎች፦ እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፥ በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጅ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፦ እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጽኑዕ ኃይል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ። ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ፦ ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ። እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዊት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፥ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። ሳኦልም ወደ እሴይ፦ በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ። እንዲህም ሆነ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፥ ሳኦልም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:15-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አገልጋዮቹም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃይሃል፤ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በገና መደርደር የሚያውቅ ሰው ፈልገን እንድናመጣልህ እዘዘን፤ ከዚያም በኋላ ክፉ መንፈስ በሚመጣብህ ጊዜ ያ ሰው በገና ይደረድርልሃል፤ አንተም እንደገና ጤናማ ትሆናለህ።” ሳኦልም “በገና በመደርደር የታወቀ ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ “የቤተልሔም ከተማ ነዋሪ የሆነው እሴይ በገና መደርደር የሚችል ልጅ እንዳለው አይቼአለሁ ይህም ብቻ ሳይሆን ጀግና፥ መልከ ቀና፥ ብርቱ ወታደርና ንግግር ዐዋቂ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለው። ስለዚህም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞች ልኮ “የበጎች እረኛ የሆነውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው። እሴይም ዳዊትን አንድ ትንሽ የፍየል ጠቦት አስይዞ፥ እንጀራና የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ከተጫነ አንድ አህያ ጋር ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጥቶ ሥራውን ጀመረ፤ ሳኦልም በጣም ስለ ወደደው የእርሱ መሣሪያ ያዥ ጋሻጃግሬ አደረገው። ከዚያም በኋላ ሳኦል ወደ እሴይ መልእክት ልኮ “ዳዊትን ወድጄዋለሁ፤ ስለዚህ እዚህ በመቈየት ያገልግለኝ” አለው። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንሥቶ ይደረድራል፤ ክፉውም መንፈስ ለቆት ስለሚሄድ ሳኦል እየተሻለው እንደገና ጤናማ ይሆናል።
1 ሳሙኤል 16:15-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፥ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።” ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሳኦል፥ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ፥ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፥ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። ከዚያም ሳኦል፥ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ። ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ተልኮ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፥ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።