1 ሳሙኤል 16:11-14
1 ሳሙኤል 16:11-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው። ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።
1 ሳሙኤል 16:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳሙኤልም እሴይን፦ የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም፦ ታናሹ ገና ቀርቶአል፥ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን፦ እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው። ልኮም አስመጣው፥ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም፦ ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።
1 ሳሙኤል 16:11-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳሙኤልም እሴይን፥ “ልጆችህ እኒህ ብቻ ናቸው?” አለው። እርሱም፥ “ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል” አለ። ሳሙኤልም እሴይን፥ “እርሱ እስኪመጣ ድረስ ለማዕድ አንቀመጥምና ልከህ አስመጣው” አለው። ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዐይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “ይህ መልካም ነውና ተነሥተህ ዳዊትን ቅባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስጨነቀው።
1 ሳሙኤል 16:11-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ታዲያ ሌሎች ልጆች የሉህምን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም “የሁሉ ታናሽ የሆነ አንድ ልጅ አለ፤ እርሱ ግን ወደ በግ እረኝነት ሄዶአል” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም “እርሱን አስጠርተህ አምጣው፤ እርሱ ሳይመጣ መሥዋዕት አናቀርብም” አለው። ስለዚህም እሴይ ልኮ አስጠራው፤ እርሱ ቀይ፥ መልከ መልካምና ዐይኖቹ የሚያበሩ ጤናማ ወጣት ነበር፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን “የመረጥኩት ሰው ይህ ነውና ተነሥተህ እርሱን ቀባው!” አለው። ሳሙኤልም በወይራ ዘይት የተሞላውን ቀንድ ወስዶ ዳዊትን በወንድሞቹ ፊት ቀባው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት አደረበት፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ከእርሱ አልተለየም፤ ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ተመለሰ። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ተለየ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር፤
1 ሳሙኤል 16:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ቀጥሎም እሴይን፥ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም፥ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም እሴይን፥ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥም” አለው። ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፥ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። ጌታም፥ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቀባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የጌታ መንፈስ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ ራማ ተመለሰ። የጌታ መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከጌታ ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።