1 ሳሙኤል 13:1-15

1 ሳሙኤል 13:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሳኦ​ልም በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ከነ​ገሠ ሁለት ዓመት ሆነው፥ ያን​ጊ​ዜም ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎ​ችን ከእ​ስ​ራ​ኤል መረጠ፤ ሁለ​ቱም ሺህ በማ​ኪ​ማ​ስና በቤ​ቴል ተራራ ከሳ​ኦል ጋር ነበሩ፤ አን​ዱም ሺህ በብ​ን​ያም ገባ​ዖን ከልጁ ከዮ​ና​ታን ጋር ነበሩ፤ የቀ​ረ​ው​ንም ሕዝብ እያ​ን​ዳ​ን​ዱን ወደ ድን​ኳኑ አሰ​ና​በተ። ዮና​ታ​ንም በኮ​ረ​ብ​ታው የነ​በ​ሩ​ትን የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን ጭፍራ መታ፤ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ያን ሰሙ፤ ሳኦ​ልም፦ እስ​ራ​ኤል ይስሙ ብሎ በሀ​ገሩ ሁሉ ቀንደ መለ​ከት ነፋ። እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ ሳኦል የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግ​ሞም እስ​ራ​ኤል በፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ዘንድ እንደ በረቱ ሰሙ፤ ሕዝ​ቡም ደን​ፍ​ተው ሳኦ​ልን ለመ​ከ​ተል ወደ ጌል​ጌላ ተሰ​በ​ሰቡ። ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ከእ​ስ​ራ​ኤል ጋር ለመ​ዋ​ጋት ተሰ​በ​ሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረ​ገ​ሎች፥ ስድ​ስት ሺህም ፈረ​ሰ​ኞች፥ በባ​ሕ​ርም ዳር እን​ዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥ​ተ​ውም ከቤ​ቶ​ሮን በአ​ዜብ በኩል በማ​ኪ​ማስ ሰፈሩ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሰዎች ወደ እነ​ርሱ መሄድ እን​ደ​ሚ​ያ​ስ​ጨ​ን​ቃ​ቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋ​ሻና በግ​ንብ፥ በገ​ደ​ልና በቋ​ጥኝ፥ በጕ​ድ​ጓ​ድም ውስጥ ተሸ​ሸጉ። ዮር​ዳ​ኖ​ስ​ንም ተሻ​ግ​ረው ወደ ጋድና ወደ ገለ​ዓድ ምድር የሄዱ አሉ፤ ሳኦል ግን ገና በጌ​ል​ጌላ ነበረ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ ፈር​ተው እር​ሱን መከ​ተ​ልን ትተው ተበ​ተኑ። ሳኦ​ልም ሳሙ​ኤል እንደ ቀጠ​ረው ጊዜ ሰባት ቀን ቈየ፤ ሳሙ​ኤል ግን ወደ ጌል​ጌላ አል​መ​ጣም፤ ሕዝ​ቡም ከእ​ርሱ ተለ​ይ​ተው ተበ​ታ​ተኑ። ሳኦ​ልም፥ “የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕ​ትና የደ​ኅ​ን​ነት መሥ​ዋ​ዕት አም​ጡ​ልኝ” አለ። የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ው​ንም መሥ​ዋ​ዕት አሳ​ረገ። የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ው​ንም መሥ​ዋ​ዕት ማሳ​ረግ በፈ​ጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙ​ኤል መጣ፤ ሳኦ​ልም እን​ዲ​ባ​ር​ከው ሊገ​ና​ኘው ወጣ። ሳሙ​ኤ​ልም፥ “ያደ​ረ​ግ​ኸው ምን​ድን ነው?” አለ። ሳኦ​ልም፥ “ሕዝቡ ከእኔ ተለ​ይ​ተው እንደ ተበ​ታ​ተኑ፥ አን​ተም በነ​ገ​ር​ኸኝ መሠ​ረት በቀ​ጠ​ሮው ቀን እን​ዳ​ል​መ​ጣህ፥ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ወደ ማኪ​ማስ እንደ ተሰ​በ​ሰቡ አየሁ፤ ስለ​ዚህ፦ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን አሁን ወደ እኔ ወደ ጌል​ጌላ ይወ​ር​ዱ​ብ​ኛል፤ እኔም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፊት አል​ለ​መ​ን​ሁም አልሁ፤ ስለ​ዚ​ህም ደፍሬ የሚ​ቃ​ጠል መሥ​ዋ​ዕ​ትን አሳ​ረ​ግሁ” አለ። ሳሙ​ኤ​ልም ሳኦ​ልን፥ “በድ​ለ​ኻል፤ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያዘ​ዘ​ህን ትእ​ዛ​ዙን አል​ጠ​በ​ቅ​ህ​ምና፤ ዛሬ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥ​ት​ህን በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ለዘ​ለ​ዓ​ለም አጽ​ን​ቶ​ልህ ነበር። ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲያ ግን መን​ግ​ሥ​ትህ አይ​ጸ​ናም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መር​ጦ​አል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ያዘ​ዘ​ህን አል​ጠ​በ​ቅ​ህ​ምና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በሕ​ዝቡ ላይ ንጉ​ሥን ያነ​ግ​ሣል” አለው። ሳሙ​ኤ​ልም ከጌ​ል​ጌላ ተነ​ሥቶ መን​ገ​ዱን ሄደ፤ የቀ​ሩ​ትም ሕዝብ ሳኦ​ልን ተከ​ት​ለው ሰል​ፈ​ኞ​ቹን ሊገ​ናኙ ሄዱ። ከጌ​ል​ጌ​ላም ተነ​ሥ​ተው ወደ ብን​ያም ገባ​ዖን መጡ፤ ሳኦ​ልም ከእ​ርሱ ጋር የነ​በ​ሩ​ትን ሕዝብ ቈጠረ፤ ስድ​ስት መቶም የሚ​ያ​ህሉ ሰዎች ነበሩ።

1 ሳሙኤል 13:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ እስራኤልንም አርባ ሁለት ዓመት ገዛ። ሳኦል ከእስራኤል ሦስት ሺሕ ሰዎች መረጠ። ሁለቱ ሺሕ በማክማስና በኰረብታማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋራ፣ አንዱ ሺሕ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋራ ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አሰናበተ። ዮናታን ጌባዕ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፣ “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሪቱ ሁሉ መለከት አስነፋ። ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺሕ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺሕ ፈረሰኞች ቍጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየእሾኽ ቍጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጕድጓዱ ሁሉ ተደበቁ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ ዐብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊቀበለው ወጣ። ሳሙኤልም፣ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰራዊቱ መበታተኑን፣ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፣ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤ ‘ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም’ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቷል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።” ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።

1 ሳሙኤል 13:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፥ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፥ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ። ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፥ ሳኦልም፦ ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ። እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፥ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፥ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፥ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ። ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቁጥቋጦ በገደልና በግንብ በጉድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ። ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፥ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፥ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ። ሳኦልም፦ የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ። ሳሙኤልም፦ ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም፦ ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፥ ሰለዚህ፦ ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፥ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ አላበጀህም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፥ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበር። አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፥ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፥ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው። ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከትለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፥ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቆጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።

1 ሳሙኤል 13:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሳኦል ሲነግሥ ዕድሜው 30 ዓመት ነበር፤ በእስራኤልም ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ከእስራኤል ሕዝብ መካከል የተውጣጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን መረጠ፤ ከእነርሱ መካከል ሁለቱን ሺህ በሚክማስና በቤትኤል በሚገኘው ኮረብታማ አገር ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ መደበ፤ አንዱን ሺህ ሰዎች ደግሞ ከልጁ ከዮናታን ጋር በማሰለፍ በብንያም ነገድ ግዛት ውስጥ ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ኮረብታማ አገር ላከ፤ ከዚህ የተረፉትን ሌሎች ሰዎች ግን ወደየቤታቸው አሰናበተ። ዮናታን ጌባዕ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጣለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ይህን ወሬ ሰሙ፤ ሳኦልም መልእክተኞችን ልኮ በሀገሩ ሁሉ እምቢልታ በማስነፋት ዕብራውያን ለጦርነት ጠራ። ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ድል እንዳደረገ እስራኤላውያን ሰሙ፤ እስራኤላውያንም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ዐወቁ፤ ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ከሳኦል ጋር የሚሰለፉ መሆናቸውን ለመግለጥ በጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያንም እስራኤላውያንን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ እነርሱም ከሠላሳ ሺህ የጦር ሠረገሎችና ከስድስት ሺህ ፈረሰኞች ጋር ብዛቱ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛ ሠራዊት ነበራቸው፤ ሄደውም በቤትአዌን በስተምሥራቅ ሚክማስ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መሸጉ። እስራኤላውያን ሁኔታው አስጊ መሆኑን ባዩና ሠራዊቱም መዋከቡን በተመለከቱ ጊዜ በዋሻ፥ በሾኽ ቊጥቋጦ፥ በአለቶች መካከል በጒድጓዶችና በጒድባ ውስጥ ተሸሸጉ፤ ከዕብራውያን መካከል አንዳንዶቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ግዛቶች ሄዱ። ሳኦል ግን እስከዚህ ጊዜ ድረስ በጌልገላ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሠራዊት ከፍርሃት የተነሣ ይንቀጠቀጥ ነበር፤ እንዲሁ ያደርግ ዘንድ ሳሙኤል ባዘዘው መሠረት፤ ሳኦል እስከ ሰባት ቀን ድረስ የሳሙኤልን መምጣት ሲጠብቅ ቈየ፤ ይሁን እንጂ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሳሙኤል ወደ ጌልጌላ አልመጣም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ የሳኦል ሰዎች ሳኦልን በመክዳት ማፈግፈግ ጀመሩ፤ ስለዚህም ሳኦል ሕዝቡን “የሚቃጠለውንና ለደኅንነት የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕት አምጡልኝ” ብሎ በማዘዝ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ይህንንም መሥዋዕት የማቅረቡን ሥርዓት እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ ሳሙኤል ደረሰ፤ ሳኦልም ወጥቶ አቀባበል አደረገለት፤ ሳሙኤል ግን “ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሕዝቡ ሊከዱኝ ተቃርበው ነበር፤ አንተም በቀጠርከኝ ሰዓት ሳትመጣ ቀረህ፤ ከዚህም በላይ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በሚክማስ ተሰለፉ፤ ስለዚህም ‘ፍልስጥኤማውያን ገና በጌልገላ ሳለሁ አደጋ ሊጥሉብኝ ነው የእግዚአብሔርንም ርዳታ ገና አለመንኩም’ ብዬ አሰብኩ፤ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚገባኝም ተረዳሁ።” ሳሙኤልም ሲመልስለት እንዲህ አለው፤ “ይህ የሞኝነት አሠራር ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልፈጸምክም፤ ትእዛዙን ብትፈጽም ኖሮ አንተና ዘሮችህ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንድትነግሡ ዛሬ መንግሥትህን ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ ዘላቂ አይሆንም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ ስላልጠበቅህ እርሱን በሕዝቡ ላይ መሪ ይሆን ዘንድ ቀብቶታል።” ሳሙኤልም ከጌልጌላ ተነሥቶ ሄደ፤ ሳኦልም ከወታደሮቹ ጋር ለመደባለቅ ሲሄድ የቀሩት ሰዎች ተከተሉት፤ ከጌልገላም ተነሥተው በብንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ሄዱ፤ ሳኦልም ሠራዊቱን በቈጠረ ጊዜ ብዛታቸው ስድስት መቶ ሆኖ ተገኘ፤

1 ሳሙኤል 13:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሳኦል በእስራኤልም ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ እንዲህ ሆነ፤ ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱ ሺህ በማክማስና በተራራማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፥ አንዱ ሺህ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ ድንኳኖቻቸው እንዲሄዱ አሰናበተ። ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፥ “ዕብራውያን ይስሙት!” በማለት በሀገሩ ሁሉ መለከት አስነፋ። እስራኤላውያን ሁሉ፥ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ የተጠሉ ሆኑ” የሚለውን ወሬ ሰሙ። ሕዝቡም ከሳኦል ጋር ለመሰለፍ ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያን ሠላሳ ሺህ ሠረገሎች፥ ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ቁጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሠራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን ያሉበት ሁኔታ እጅግ አስጊ መሆኑንና ሠራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፥ በየዋሻውና በየቁጥቋጦው፥ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጉድጓዱ ሁሉ ተሸሸጉ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበር፤ አብሮት የተሰለፈው ሠራዊት ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰዎች መበታተን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፥ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ፥ ወዲያውኑ ሳሙኤል ደረሰ፤ እርሱም ሊቀበለው ወጣ። ሳሙኤል ግን “ያደረግኸው ነገር ምንድነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ሠራዊቱ መበታተኑን፥ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፥ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የጌታን ርዳታ አልለመንሁም፥ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ። ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ ጌታ የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ባጸናልህ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ ጌታ እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የጌታን ትእዛዝ ባለመጠበቅህም፥ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።” ከዚያ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ሄደ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፤ ስድስት መቶ ያህል ነበሩ።