1 ሳሙኤል 11:1-15
1 ሳሙኤል 11:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ መጣ፤ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፥ “አሞናዊውን ናዖስን ቃል ኪዳን አድርግልን፤ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። አሞናዊው ናዖስም፦“ ቀኝ ዐይናችሁን ብታወጡ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብን አደርጋለሁ” አላቸው። የኢያቢስም ሰዎች፥ “ወደ እስራኤል ሀገር ሁሉ መልእክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቈይልን፤ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ገባዖን መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። እነሆም፥ ሳኦል ከእርሻው አርፍዶ መጣ፤ ሳኦልም፥ “ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው?” አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት። ይህንም ነገር በሰማ ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ፤ በእነርሱም ላይ ተቈጣ። ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ በየብልታቸው ቈራረጣቸው፤ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልእክተኞቹ እጅ ላከና፥ “ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግበታል” አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፤ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ጮኹ። በባማ ባለው በቤዜቅም ቈጠራቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ። የመጡትንም መልእክተኞች፥ “የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች፦ ነገ ፀሐይ በተኰሰ ጊዜ ድኅነት ይሆንላችኋል በሉአቸው” አሉአቸው። መልእክተኞችም ወደ ከተማዪቱ መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፤ ደስም አላቸው። የኢያቢስም ሰዎች፦ ለአሞናዊው ናዖስ “ነገ እንወጣላችኋለን፤ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን” አሉት። በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፤ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፤ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፤ የቀሩትም ተበተኑ፤ ከውስጣቸውም ሁለት በአንድ ላይ ሆነው አልተገኙም። ሕዝቡም ሳሙኤልን፥ “ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማን ናቸው? እነዚያን ሰዎች አውጡአቸውና እንግደላቸው” አሉት። ሳኦልም፦“በዚያች ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤል ድኅነትን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም” አለ። ሳሙኤልም ሕዝቡን፥ “ኑ፤ ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ በዚያም መንግሥቱን እናጽና” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን ቀብቶ በእግዚአብሔር ፊት በጌልጌላ አነገሠው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የእህል ቍርባንና የሰላም መሥዋዕት አቀረበ፤ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።
1 ሳሙኤል 11:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ኢያቢስ ገለዓድን ከበባት፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፣ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፣ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። አሞናዊው ናዖስ፣ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። የኢያቢስም ሽማግሌዎች፣ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ፣ ለአንተ እንገዛለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ፣ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከዕርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ እጅግ ተቈጣ። ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቍጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺሕ፣ ከይሁዳም ሠላሳ ሺሕ ነበር። ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፣ “ለኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች፣ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለኢያቢስ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ በደስታ ፈነደቁ። ለአሞናውያንም፣ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው። በማግስቱም ሳኦል ሰራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል፣ የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳ ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። ሕዝቡ ሳሙኤልን፣ “ ‘ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል!’ ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት። ሳኦል ግን፣ “ይህ ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን የታደገበት ቀን ስለሆነ፣ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፣ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውን እናጽና” አለ። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በእግዚአብሔር ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ ታላቅ በዓል አደረጉ።
1 ሳሙኤል 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ ወጣ፥ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፥ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፦ ቃል ኪዳን አድርግልን፥ እኛም እንገዛልሃለን አሉት። አሞናዊውም ናዖስ፦ ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብ አደረጋለሁ አላቸው። የኢያቢስም ሽማግሌዎች፦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ መልክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቆይልን፥ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን አሉት። መልክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፥ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። እነሆም፥ ሳኦል በሬዎቹን ተከትሎ ከእርሻው መጣ፥ ሳኦልም፦ ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው? አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት። ይህንም ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፥ ቁጣውም እጅግ ነደደ። ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ ቆራረጣቸው፥ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልክተኞቹ እጅ ሰደደና፦ ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግ አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ወጡ። በቤዜቅም ቆጠራቸው፥ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ። የመጡትንም መልክተኞች፦ የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች፦ ነገ ፀሐይ በተኮሰ ጊዜ ማዳን ይሆንላችኋል በሉአቸው አሉአቸው። መልክተኞችም መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፥ ደስም አላቸው። የአያቢስም ሰዎች፦ ነገ እንወጣላችኋለን፥ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን አሉ። በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፥ ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፥ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፥ የቀሩትም ተበተኑ፥ ሁለትም በአንድ ላይ ሆነው አልቀሩላቸውም። ሕዝቡም ሳሙኤልን፦ ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማናቸው? አውጡአቸውና እንግደላቸው አሉት። ሳኦልም፦ ዛሬ እግዚአብሔር ለእስራኤል ማዳን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ። ሳሙኤልም ሕዝቡን፦ ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድ፥ በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፥ በዚያም ሳኦልን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ አነገሡት፥ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፥ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።
1 ሳሙኤል 11:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከአንድ ወር በኋላ የዐሞን ንጉሥ ናዖስ በገለዓድ ግዛት በምትገኘው በያቤሽ ከተማ ላይ ሠራዊቱን በማዝመት ከበባት፤ የያቤሽም ሰዎች ናዖስን “ከእኛ ጋር የውል ስምምነት አድርግ፤ እኛም የአንተ አገልጋዮች እንሆናለን” አሉት። ናዖስም “ከእናንተ ጋር የውል ስምምነት ማድረግ የምችልበት አንድ ዐይነት ግዴታ አለ፤ ይኸውም የእያንዳንዱን ሰው ቀኝ ዐይን በማውጣት በእስራኤላውያን ላይ አሳፋሪ ውርደት አመጣለሁ” ሲል መለሰላቸው። የያቤሽ መሪዎችም “ወደ መላው የእስራኤል ምድር መልእክተኞች እስክንልክ ድረስ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ እኛን የሚታደገን ካጣን ለአንተ እጃችንን እንሰጣለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ ደረሱ፤ ወሬውንም በተናገሩ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። ሳኦል በዚህ ጊዜ ጥንድ በሬዎቹን ይዞ ከዋለበት እርሻ በመመለስ ላይ ነበር፤ እርሱም “ምንድን ነው ነገሩ? ሰው ሁሉ የሚያለቅሰው ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፤ እነርሱም ከያቤሽ የመጡ መልእክተኞች የሚሉትን ወሬ ነገሩት። ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኀይል ወረደ፤ የሳኦልም ቊጣ እጅግ ገነፈለ። ጥንዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፤ የሥጋውንም ቊራጭ ሁሉ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ ጦርነት የማይወጣ ሰው ቢኖር በሬዎቹ እንደዚህ ይቈራረጡበታል!” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር መልእክተኞችን ወደ መላው የእስራኤል ምድር ላከ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈራ፤ አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም በአንድነት ወጡ። ሳኦልም ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰበሰባቸው፤ የቊጥራቸውም ብዛት ከእስራኤል የመጡት ሦስት መቶ ሺህ ሲሆን ከይሁዳ የመጡት ሠላሳ ሺህ ነበር። ከያቤሽ የመጡትንም መልእክተኞች “ነገ ከቀትር በፊት የምናድናቸው መሆኑን ለሕዝባችሁ ንገሩ” አሉአቸው። መልእክቱንም ለያቤሽ ሰዎች በነገሩ ጊዜ የያቤሽ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ። የያቤሽም ሰዎች አሞናውያንን “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን እናንተም በእኛ ላይ የምትፈልጉትን አድርጉ” አሉአቸው። በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ከፈለ፤ ከማለዳ ጀምሮ ባለው ጊዜ በአሞናውያን ሰፈር ላይ አደጋ ጥለው ፀሐይ እስኪሞቅ ድረስ ፈጁአቸው፤ ከእልቂት የተረፉትም ተበታትነው ለየብቻቸው ሸሹ። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሳሙኤልን “ሳኦል በእኛ ላይ አይነግሥብንም ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው? እነርሱን አሳልፈህ ስጠንና እንግደላቸው!” አሉት። ሳኦል ግን “በዛሬው ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ስላዳነ ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ። ሳሙኤልም “ሁላችንም ወደ ጌልጌላ እንሂድና ሳኦል ንጉሣችን መሆኑን እንደገና በይፋ እናረጋግጥ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልጌላ ሄደው በእግዚአብሔር ፊት የሳኦልን ንጉሥነት አጸደቁ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዓሉንም ሳኦልና መላው ሕዝብ በታላቅ ደስታ አከበሩት።
1 ሳሙኤል 11:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ያቢሽ ገለዓድን ከበባት፤ የያቢሽም ሰዎች ሁሉ ናዖስን፥ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። አሞናዊው ናዖስ ግን፥ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። የያቢሽም ሽማግሌዎች፥ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ ለአንተ እንገዛለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከእርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፥ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የያቢሽ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ቁጣውም እጅግ ነደደ። ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቆራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፥ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቆራረጣል!” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከጌታ ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሠራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቁጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺህ፥ ከይሁዳም ሠላሳ ሺህ ነበር። ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፥ “ለያቢሽ ገለዓድ ሰዎች፥ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለያቢሽ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ተደሰቱ። የያቢሽም ሰዎች፥ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው። በማግስቱ ሳኦል ሠራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳን ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። ሕዝቡ ሳሙኤልን፥ “ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል! ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት። ሳኦል ግን፥ “ይህ ዕለት ጌታ እስራኤልን የታደገበት ቀን ሰለሆነ፥ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፥ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውንም እናጽና” አለ። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በጌታ ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት በጌታ ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ በታላቅ ደስታ አከበሩት።