1 ሳሙኤል 1:19-28
1 ሳሙኤል 1:19-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም ጧት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤ እግዚአብሔርም ዐሰባት፤ ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል አለችው። ሰውየውም ሕልቃና ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ። ሐና ግን አልሄደችም፤ እርሷም ባሏን፣ “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄ በእግዚአብሔር ፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” አለችው። ባሏ ሕልቃናም፣ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥዪው ድረስ እዚሁ ቈዪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሐና ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች። ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፣ በሴሎ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፣ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ። ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት። ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር ስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ። ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ። ስለዚህ እኔም ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገደ።
1 ሳሙኤል 1:19-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፥ እግዚአብሔርም አሰባት፥ የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፥ እርስዋም፦ ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ። ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም፦ ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፥ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው። ባልዋም ሕልቃና፦ በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፥ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች። ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፥ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ። ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት። እርስዋም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፥ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፥ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።
1 ሳሙኤል 1:19-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱም ሕልቃናና ቤተሰቡ በማለዳ ተነሥተው ለእግዚአብሔር ከሰገዱ በኋላ በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ፤ ሕልቃናም ከሚስቱ ከሐና ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እግዚአብሔርም አስታወሳት፤ ወዲያውኑ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እርስዋም “ከእግዚአብሔር ለምኜ ያገኘሁት ነው” ስትል ስሙን “ሳሙኤል” አለችው። ሕልቃና ከቤተሰቡ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕትና ስእለት ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ወደ ሴሎ ወጣ። “ልጄ ጡት በሚተውበት ጊዜ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ወደሚኖርበት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወዲያውኑ እወስደዋለሁ” ብላ ለባልዋ ነግራው ስለ ነበር ሐና በዚህ ጊዜ አብራ አልወጣችም፤ ሕልቃናም “ጥሩ ነው፤ መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥይውም ድረስ በቤት መቈየት ትችያለሽ፤ እግዚአብሔር የሰጠሽን የተስፋ ቃል ይፈጽምልሽ” ሲል መለሰላት፤ ስለዚህም ሐና በቤት ተቀምጣ ልጇን ታሳድግ ጀመር። ጡት ካስጣለችውም በኋላ ወደ ሴሎ ይዛው ወጣች፤ ከእርሱም ጋር የሦስት ዓመት ኰርማ ዐሥር ኪሎ ዱቄትና አንድ አቁማዳ ሙሉ የወይን ጠጅ ይዛ ሄደች፤ ሳሙኤልንም ገና በልጅነቱ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ወሰደችው፤ ኰርማውንም ካረዱ በኋላ ሕፃኑን ወደ ዔሊ አቀረቡት፤ ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፥ ዕድሜህን ያርዝመውና አንድ ጊዜ እዚህ በፊትህ ቆሜ ወደ እግዚአብሔር ስጸልይ ያየኸኝ ሴት እኔ ነኝ፤ የጸለይኩትም እግዚአብሔር ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ነበር፤ እግዚአብሔርም በጠየቅሁት መሠረት ይህን ወንድ ልጅ ሰጠኝ። እኔም ደግሞ እርሱን ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ እንዲሆን አድርጌአለሁ፤ ስለዚህም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።” ከዚያም በኋላ በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
1 ሳሙኤል 1:19-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማልደውም ተነሥተው ለእግዚአብሔር ሰግደው ሄዱ፤ ወደ ቤታቸውም ወደ አርማቴም ደረሱ፤ ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤ ፀነሰችም። የመውለጃዋም ወራት በደረሰ ጊዜ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም፥ “ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ስሙን “ሳሙኤል” ብላ ጠራችው። ሰውዬውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን፥ የምድሩንም ዐሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ። ሐና ግን ከእርሱ ጋር አልወጣችም። ለባልዋም፥ “ሕፃኑን ጡት እስከ አስጥለው፥ ከእኔም ጋር እስኪወጣና በእግዚአብሔር ፊት እስኪታይ ድረስ አልወጣም፤ በዚያም ለዘለዓለም ይኖራል” ብላዋለችና። ባልዋም ሕልቃና፥ “በዐይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፤ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ከአፍሽ የወጣውን ያጽና” አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ ተቀመጠች። እርስዋም ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ እንጀራ፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወጣች። በሴሎም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባች። ልጃቸውም ከእነርሱ ጋር ነበረ። በእግዚአብሔርም ፊት አቀረቡት ፤ አባቱም በየዓመቱ ለእግዚአብሔር የሚሠዋውን መሥዋዕት ሠዋ። ሕፃኑንም አቀረበው፤ ወይፈኑንም አረደ፤ እናቱም ሐና ሕፃኑን ወደ ዔሊ አገባችው። እርስዋም አለች፥ “ጌታዬ ሆይ! በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በፊትህ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። ስለዚህ ልጅ ተሳልሁ፤ ጸለይሁም፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ዕድሜውን ሙሉ እግዚአብሔርን ያገለግል ዘንድ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ።”
1 ሳሙኤል 1:19-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በማግስቱ ጠዋት ተነሥተው በጌታ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ ጌታም አሰባት፤ ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ “ከጌታ ለምኜዋለሁ” ስትል ስሙን “ሳሙኤል” ብላ ጠራችው። ሰውዬውም ሕልቃና ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ለጌታ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት፥ ስእለቱንም ለማድረስ ወደ ሴሎ ወጣ። ሐና ግን አልሄደችም፤ ምክንያቱም ለባሏ፥ “ሕፃኑ ጡት እንደተወ፥ በጌታ ፊት ቀርቦ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ እንዲኖር፥ አመጣዋለሁ” ብላው ነበርና ነው። ባሏ ሕልቃናም፥ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥይው ድረስ እዚሁ ቆይ፤ ብቻ ጌታ ቃሉን ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሴቲቱ ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች። ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፥ በሴሎ ወዳለው ወደ ጌታ ቤት አመጣችው፤ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ። ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት። እርሷም እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! እዚህ ቦታ ላይ በፊትህ ቆማ ወደ ጌታ ስትጸልይ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። ስለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ ጌታም የለመንሁትን ሰጠኝ። ስለዚህ እኔም ለጌታ እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለጌታ የተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያ ለጌታ ሰገደ።