1 ሳሙኤል 1:1-19
1 ሳሙኤል 1:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ስሙም፥ የናሲብ ልጅ የቴቆ ልጅ፥ የኤልዩ ልጅ ፥ የኢያርምያል ልጅ፥ ኤፍራታዊው ሕልቃና ነበረ። ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና፥ የሁለተኛዪቱም ስም ፍናና ነበረ፤ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፤ ለሐና ግን ልጆች አልነበሩአትም። ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ፥ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው ከአርማቴም በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ። ሕልቃናም የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜ ለሚስቱ ለፍናናና ለልጆችዋ ሁሉ ዕድል ፋንታቸውን ሰጣቸዉ። ለሐናም ልጅ ስላልነበራት አንድ ዕድል ፋንታ ሰጣት፤ ሕልቃናም ከዚያችኛይቱ ይልቅ ሐናን ይወድድ ነበር። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር። እንደ መከራዋና እንደ ኀዘንዋም እግዚአብሔር ልጅ አልሰጣትም ነበር። ስለዚህም ታዝን ነበር። እግዚአብሔር ማኅፀንዋን ዘግትዋልና፥ ልጆችንም አልሰጣትምና። በየዓመቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚወጣበት ጊዜ እንዲህ ያደርግ ነበር፤ እርስዋም ትበሳጭና ታለቅስ ነበር። እህልም አትበላም ነበር። ባልዋ ሕልቃናም፥ “ሐና ሆይ!” አላት እርስዋም፥ “ጌታዬ እነሆኝ” አለችው። እርሱም፥ “ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከዐሥር ልጆች አልሻልሽምን?” አላት። በሴሎም ከበሉ በኋላ ሐና ተነሣች። በሴሎም በእግዚአብሔር ፊት ቆመች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርስዋም በልብዋ አዝና አለቀሰች፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየች። እርስዋም፥ “አዶናይ፥ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! የባርያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ ለባርያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ ዕድሜውን ሁሉ ለአንተ እሰጠዋለሁ፤ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥም አይጠጣም። ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም” ብላ ስእለት ተሳለች። ጸሎቷንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ፥ ካህኑ ዔሊ አፍዋን ይመለከት ነበር። ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። የዔሊም አገልጋይ፦ “ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ውጪ” አላት። ሐናም መልሳ እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፤ እኔስ ወራት የባሳት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ እደክማለሁና ባርያህን እንደ ኀጢአተኞች ሴቶች ልጆች አትቍጠራት።” ዔሊም፥ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤልም አምላክ ከአንቺ ጋር ይሁን የለመንሽውንም ልመና ሁሉ ይስጥሽ” ብሎ መለሰላት። እርስዋም፥ “ባርያህ በፊትህ ሞገስን አገኘች” አለችው። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች፤ ወደ ቤትዋም ገባች፤ ከባሏም ጋር በላች፤ ጠጣችም ፤ ፊቷም ከዚያ በኋላ አዘንተኛ መስሎ አልታየም። ማልደውም ተነሥተው ለእግዚአብሔር ሰግደው ሄዱ፤ ወደ ቤታቸውም ወደ አርማቴም ደረሱ፤ ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤ ፀነሰችም።
1 ሳሙኤል 1:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ የኤያሬምኤል ልጅ፣ የኢሊዩ ልጅ፣ የቶሑ ልጅ፣ የናሲብ ልጅ፣ ነበረ። እርሱም አንዲቱ ሐና፣ ሌላዪቱ ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍናና ልጆች ሲኖሯት፣ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም። ያም ሰው ሁሉን ቻይ ለሆነው ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የእግዚአብሔር ካህናት ነበሩ። ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። ሐናን ግን ይወድዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። እግዚአብሔር ማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር። ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር። ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።” ሐና ባለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምፅዋ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት። እርሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት። ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም። ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭንቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ።” ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት። እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም። በማግስቱም ጧት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤ እግዚአብሔርም ዐሰባት፤
1 ሳሙኤል 1:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፥ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ። ሁለትም ሚስቶች ነበሩት የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፥ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም። ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ። ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው። ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት፥ እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር። በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፥ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር። ባልዋም ሕልቃና፦ ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት። በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሐና ተነሳች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔርም ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች። እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፍዋን ይመለከት ነበር። ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፥ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፥ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። ዔሊም፦ ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት። ሐናም፦ ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፥ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፥ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት። ዔሊም፦ በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት። እርስዋም፦ ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች፥ በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም። ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፥ እግዚአብሔርም አሰባት፥
1 ሳሙኤል 1:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራማ ተብላ በምትጠራ ትንሽ ከተማ የሚኖር ትውልዱ ከኤፍሬም ነገድ የሆነ፥ ሕልቃና ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም የይሮሐም ልጅ የኤሊሁ የልጅ ልጅ ሲሆን፥ ኤሊሁ ደግሞ የቶሑ ልጅ የጹፍ የልጅ ልጅ ነበር፤ ሕልቃናም ሐናና ፍኒና ተብለው የሚጠሩ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍኒና ልጆች ነበሩአት፤ ሐና ግን አንድም ልጅ አልነበራትም፤ ሕልቃና በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ሴሎ ይሄድ ነበር፤ በዚያም ዘመን ሖፍኒና ፊንሐስ ተብለው የሚጠሩት የዔሊ ልጆች የእግዚአብሔር ካህናት ሆነው በሴሎ ያገለግሉ ነበር። ሕልቃና መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ ከመሥዋዕቱ ሥጋ አንድ ድርሻ ለጵኒና ይሰጣል፤ እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ድርሻ ያድላል፤ ሐናን ይወዳት ስለ ነበር እጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ቢሆንም እግዚአብሔር ልጅ ስላልሰጣት መኻን ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልጅ ስላልሰጣት ጣውንትዋ ጵኒና ሐናን የሚያስቈጣ ነገር በመፈለግ ታበሳጫት ነበር፤ ይህም ሳይቋረጥ በየዓመቱ የሚደጋገም ነገር ነበር፤ ይኸውም ወደ እግዚአብሔር ቤት በሄዱ ቊጥር ሐና እያለቀሰች ምግብ ለመብላት እምቢ እስከምትል ድረስ ጵኒና በብርቱ ታበሳጫት ነበር። ከዚህም የተነሣ ባልዋ ሕልቃና “ሐና ሆይ! ስለምን ታለቅሻለሽ? ስለምንስ አትመገቢም? ስለምንስ ዘወትር ይህን ያኽል ታዝኚአለሽ? ከዐሥር ልጆች ይልቅ እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። አንድ ቀን በሴሎ መሥዋዕት ሠውተው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች፤ ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ በር አጠገብ ተቀምጦ ነበር። እርስዋም ከልብዋ ሐዘን የተነሣ ምርር ብላ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። ሐናም እንዲህ ስትል ስእለት ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እኔን አገልጋይህን ተመልከተኝ! መከራዬንም በማየት አስበኝ! አትርሳኝም! አንድ ወንድ ልጅ ብትሰጠኝ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የተለየ እንዲሆን አደርገዋለሁ፤ ጠጒሩም ከቶ አይላጭም።” ሐና በዚህ ዐይነት ጸሎትዋን በማስረዘም ብዙ ጊዜ ስለ ቈየች፥ ዔሊ አፍዋን ይመለከት ነበር፤ ሐና ምንም ድምፅ ሳታሰማ ከንፈርዋን እያንቀሳቀሰች በልብዋ በመናገር ትጸልይ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ዔሊ በመጠጥ የሰከረች መሰለው፤ “እንዲህ ሰክረሽ የምትቈዪው እስከ መቼ ነው? ይህን ስካርሽን ወዲያ አስወግጂ!” አላት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “አይደለም ጌታዬ ሆይ! እኔ በጥልቅ ሐዘን ላይ ያለሁ ሰው ነኝ፤ ወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፤ ነገር ግን ችግሬን ለእግዚአብሔር እያቀረብኩ ነው። እኔን አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አድርገህ አትቊጠረኝ፤ ይህን ያኽል በማስረዘም የጸለይኩት መከራ የበዛብኝ ችግረኛ በመሆኔ ነው።” ዔሊም “በሰላም ሂጂ! የእስራኤል አምልክ የለመንሽውን ይስጥሽ!” አላት። እርስዋም “እኔን አገልጋይህን በጸሎትህ አስበኝ!” አለችው፤ ከዚያም ተነሥታ በመሄድ ምግብ ተመገበች፤ ሐዘንዋንም አቆመች። በማግስቱም ሕልቃናና ቤተሰቡ በማለዳ ተነሥተው ለእግዚአብሔር ከሰገዱ በኋላ በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ፤ ሕልቃናም ከሚስቱ ከሐና ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እግዚአብሔርም አስታወሳት፤
1 ሳሙኤል 1:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የይሮሐም ልጅ፥ የኤሊዩ ልጅ፥ የቶሑ ልጅ፥ የናሲብ ልጅ ሲሆን ከኤፍሬም ነገድ ነበረ። እርሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ስማቸውም አንዲቱ ሐና፥ ሁለተኛዪቱም ጵኒና ነበር። ጵኒና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም። ያም ሰው በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ የጌታ ካህናት ነበሩ። ሕልቃና መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፥ ለሚስቱ ለጵኒና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። ሐናንም ይወዳት ስለ ነበር ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ ጌታ ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። ጌታ ማሕፀኗን ስለዘጋም ጣውንቷ ሆን ብላ ታስቆጣት፥ ታበሳጫትም ነበር። ወደ ጌታ ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ ይህ በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ታበሳጫት ነበር። ባሏ ሕልቃናም እርሷን፥ “ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በጌታ ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሷም ከልቧ ኀዘን የተነሣ ምርር ብላ እያለቀሰች ወደ ጌታ ጸለየች። እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሠራዊት ጌታ ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ ለአገልጋይህም ወንድ ልጅ ብትሰጣት፥ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለጌታ እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አያርፍም።” ጸሎትዋንም ባለማቋረጥ ወደ ጌታ ባቀረበች ጊዜ፥ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። ሐናም በልቧ ትጸልይ የነበረ በመሆኑ፥ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምጿ አይሰማም ነበር፤ ስለዚህ ዔሊ እንደ ሰከረች አድርጎ ቆጠራት “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” ሲልም ዔሊ ተናገራት። ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፥ “ጌታዬ ሆይ፤ አይደለም፤ እኔስ ልቧ ክፉኛ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ የልቤን ኀዘን በጌታ ፊት አፈሰስሁ እንጂ፥ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም። ይህን ያህል ጊዜ የጸለይኩት ከባድ ከሆነው ጭንቀቴና መከራዬ የተነሣ ስለሆነ፥ አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አትቁጠረኝ።” ከዚያም ዔሊ፥ “በሰላም ሂጂ! የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ይስጥሽ!” አላት። እርሷም፥ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም ተነሥታ መንገዷን ቀጠለች፤ ምግብም በላች፤ በፊቷም ገጽ ኀዘን መታየቱ ቆመ። በማግስቱ ጠዋት ተነሥተው በጌታ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን ዐወቃት፤ ጌታም አሰባት፤