የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ጴጥሮስ 3:8-22

1 ጴጥሮስ 3:8-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። ስለዚህ፣ “ሕይወትን የሚወድድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ ምላሱን ከክፉ፣ ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል። ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤ ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤ የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።” መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።” ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው። እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እንቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።

1 ጴጥሮስ 3:8-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፤ እንደወንድሞች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፤ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻ፤ ይከተለውም፤ የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፤ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፤ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።” በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ፤ አትናወጡም፤ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና። ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።

1 ጴጥሮስ 3:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኵኦልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው። በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኃልና። ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቍኦየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።

1 ጴጥሮስ 3:8-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በቀረውስ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ፤ የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ ቊጠሩ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ደጎችና ትሑቶች ሁኑ። መርቁ እንጂ ክፉውን በክፉ ፈንታ፥ ስድብንም በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ እናንተ የተጠራችሁት ይህን በማድረግ በረከትን ለመውረስ ነው፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፦ “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ፥ ምላሱ ክፉ ነገር እንዳይናገር፥ ከንፈሮቹ ተንኰልን እንዳይናገሩ ይከልክል። ከክፉ ነገር ይራቅ፤ መልካምን ነገር ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤ የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም ጸሎታቸውን ለመስማት ተከፍተዋል፤ በክፉ አድራጊዎች ላይ ግን ጌታ የቊጣ ፊቱን ያሳያል።” መልካም ነገር ለማድረግ ብትተጉ ጒዳት የሚያደርስባችሁ ማን ነው? መልካም ነገር በማድረግ መከራን ብትቀበሉ እንኳ በረከትን ታገኛላችሁ፤ የሰዎችን ዛቻ አትፍሩ፤ አትጨነቁም። ጌታ ክርስቶስን በልባችሁ አክብሩት፤ ለሕይወታችሁም ጌታ አድርጉት፤ በእናንተ ስላለውም ተስፋ ለሚጠይቃችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ ዝግጁዎች ሁኑ። መልሳችሁ ግን በገርነትና በአክብሮት ይሁን፤ የክርስቶስ በመሆናችሁ ባላችሁ መልካም ጠባይ ላይ ክፉ የሚናገሩ ሰዎች በክፉ ንግግራቸው እንዲያፍሩ መልካም ኅሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ እናንተ ክፉ ነገርን በማድረግ መከራ ከምትቀበሉ መልካም ነገርን በማድረግ መከራ ብትቀበሉ ይሻላል። ክርስቶስም ራሱ ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ሳለ ጽድቅ ለሌለን ለእኛ በኃጢአታችን ምክንያት በማያዳግም ሁኔታ አንድ ጊዜ መከራን በመቀበል ሞቶአል፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ። በዚያው መንፈስ በእስር ቤት ወዳሉት ነፍሶች ሄዶ የምሥራቹን ቃል አበሠራቸው። እነዚህ በወህኒ ቤት የነበሩ መናፍስት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲዘጋጅ እግዚአብሔር በትዕግሥት ሲጠብቃቸው ሳለ አንታዘዝም ያሉ ናቸው። በዚያ መርከብ ውስጥ ገብተው በውሃ አማካይነት የዳኑት ቊጥራቸው ስምንት የሆነ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህም ውሃ አሁን እናንተን የሚያድን የጥምቀት ምሳሌ ነው፤ ይህ ጥምቀት የሰውነትን ዕድፍ ማስወገድ ሳይሆን ንጹሕ ኅሊናን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ልመና ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ እርሱ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ነው፤ መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ተገዝተውለታል።

1 ጴጥሮስ 3:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ እርስ በእርሳችሁ ተሳሰቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም በረከትን ልትወርሱ ተጠርታችኋል። “ሕይወትን የሚወድ መልካም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ፥ ምላሱን ከክፉ ይጠብቅ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉም ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻት፤ ይከተላትም። የጌታ ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው የተከፈቱ ናቸው፤ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።” ለመልካም ነገር ቀናኢ ብትሆኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ዛቻቸውንም አትፍሩ፤ አትታወኩም። ነገር ግን ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተም ስላለች ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በገርነትና በአክብሮት አድርጉት፤ በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ በመንቀፍ የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ መልካም ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚእብሔር ፈቃድ ከሆነ፥ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል። ክርስቶስ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኃጢአት መከራን ተቀበለ፤ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባችሁ በሥጋ ሞተ፥ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ። በዚያው መንፈስ በእስር ቤት ወዳሉት ነፍሳት ሄዶ ሰበከላቸው፤ እነዚህ ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ሲጠብቃቸው አንታዘዝም ያሉ ናቸው። በውሃ የዳኑት ጥቂት ሲሆኑ እነርሱም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይህ ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ እናንተን ያድናል፤ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ ሳይሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የበጎ ሕሊና ልመና ነው። እርሱም ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም ተገዝተውለታል።