1 ነገሥት 15:1-24

1 ነገሥት 15:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የና​ባጥ ልጅ ኢዮ​ር​ብ​ዓም በነ​ገሠ በዐ​ሥራ ስም​ን​ተ​ኛው ዓመት የሮ​ብ​ዓም ልጅ አብያ በይ​ሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እና​ቱም መዓካ የተ​ባ​ለች የአ​ቤ​ሴ​ሎም ልጅ ነበ​ረች። ከእ​ር​ሱም አስ​ቀ​ድሞ ባደ​ረ​ገው በአ​ባቱ ኀጢ​አት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአ​ም​ላኩ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጋር ፍጹም አል​ነ​በ​ረም። ነገር ግን ልጁን ከእ​ርሱ በኋላ ያስ​ነሣ ዘንድ፥ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ም​ንም ያጸና ዘንድ አም​ላኩ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስለ ዳዊት በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም መብ​ራ​ትን አደ​ረ​ገ​ለት፤ ከኬ​ጥ​ያ​ዊው ከኦ​ርዮ ነገር በቀር ዳዊት በዘ​መኑ ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ቅን ነገ​ርን አድ​ርጎ ነበ​ርና፥ ካዘ​ዘ​ውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላ​ለም ነበ​ርና። በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓ​ምና በሮ​ብ​ዓም መካ​ከል በዘ​መ​ና​ቸው ሁሉ ጠብ ነበረ። የቀ​ረ​ውም የአ​ብያ ነገር፥ ያደ​ረ​ገ​ውም ሁሉ፥ በይ​ሁዳ ነገ​ሥ​ታት ታሪክ መጽ​ሐፍ እነሆ፥ የተ​ጻፈ አይ​ደ​ለ​ምን? በአ​ብ​ያና በኢ​ዮ​ር​ብ​አም መካ​ከል ሰልፍ ነበረ። ኢዮ​ር​ብ​ዓም በነ​ገሠ በሃያ አራ​ተኛ ዓመቱ አብያ ከአ​ባ​ቶቹ ጋር አን​ቀ​ላፋ፤ በዳ​ዊ​ትም ከተማ ቀበ​ሩት። ልጁም አሳ በፋ​ን​ታው ነገሠ። በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓም በሃያ አራ​ተ​ኛው ዓመት አሳ በይ​ሁዳ ላይ ነገሠ። በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እና​ቱም ሐና የተ​ባ​ለች የአ​ቤ​ሴ​ሎም ልጅ ነበ​ረች። አሳም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ቅን ነገ​ርን አደ​ረገ። ከሀ​ገ​ሩም የጣ​ዖ​ታ​ትን ምስል ሁሉ አስ​ወ​ገደ፥ አባ​ቶ​ቹም የሠ​ሩ​አ​ቸ​ውን ጣዖ​ታ​ትን ሁሉ አጠፋ። የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀድ ጣዖ​ታ​ትን ስለ ሠራች እና​ቱን ሐናን እቴጌ እን​ዳ​ት​ሆን ሻራት፤ አሳም የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀ​ዱን አስ​ቈ​ረ​ጠው፥ በቄ​ድ​ሮ​ንም ፈፋ አጠ​ገብ በእ​ሳት አቃ​ጠ​ለው። ነገር ግን በኮ​ረ​ብ​ቶች ላይ ያሉ​ትን መስ​ገ​ጃ​ዎች አላ​ራ​ቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘ​መኑ ሁሉ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጋር ፍጹም ነበረ። አባቱ የቀ​ደ​ሰ​ው​ንና እር​ሱም የቀ​ደ​ሰ​ውን ወር​ቅና ብር፥ ዕቃ​ው​ንም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት አገ​ባው። አሳና የእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ ባኦስ በዘ​መ​ና​ቸው ሁሉ ሲዋጉ ኖሩ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ ባኦስ በይ​ሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይ​ሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እን​ዳ​ይ​ወጣ ወደ እር​ሱም ማንም እን​ዳ​ይ​ገባ አድ​ርጎ ራማን ሠራት። አሳም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤትና በን​ጉሥ ቤተ መዛ​ግ​ብት የተ​ገ​ኘ​ውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለአ​ገ​ል​ጋ​ዮቹ ሰጣ​ቸው፤ ንጉ​ሡም አሳ በደ​ማ​ስቆ ለተ​ቀ​መ​ጠው ለአ​ዚን ልጅ ለጤ​ቤ​ር​ማን ልጅ ለሶ​ርያ ንጉሥ ለወ​ልደ አዴር፥ “በእ​ኔና በአ​ንተ መካ​ከል በአ​ባ​ቴና በአ​ባ​ትህ መካ​ከል ቃል ኪዳን ጸን​ቶ​አል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረ​ከት ልኬ​ል​ሃ​ለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እን​ዲ​ርቅ ሄደህ ከእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ ከባ​ኦስ ጋር ያለ​ህን ቃል ኪዳን አፍ​ርስ” ብሎ ላከ። ወልደ አዴ​ርም ለን​ጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠ​ራ​ዊ​ቱ​ንም አለ​ቆች በእ​ስ​ራ​ኤል ከተ​ሞች ላይ ሰድዶ ኢና​ን​ንና ዳንን፥ አቤ​ል​ቤ​ት​መ​ዓ​ካ​ንና ኬኔሬ​ትን ሁሉ የን​ፍ​ታ​ሌ​ም​ንም ሀገር ሁሉ መታ። ባኦ​ስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥ​ራት ትቶ ወደ ቴርሳ ተመ​ለሰ። ንጉ​ሡም አሳ በይ​ሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አል​ነ​በ​ረም፥ ንጉሡ ባኦ​ስም የሠ​ራ​በ​ትን የራ​ማን ድን​ጋ​ይና እን​ጨት ወሰደ፤ የይ​ሁ​ዳም ንጉሥ አሳ የብ​ን​ያ​ም​ንና የመ​ሴ​ፋን ኮረ​ብታ ሠራ​በት። የቀ​ረ​ውም የአሳ ነገር ሁሉ ብርቱ ሥራ​ዎ​ቹም ሁሉ፥ ያደ​ረ​ገ​ውም ሁሉ፥ በይ​ሁዳ ነገ​ሥት ታሪክ የተ​ጻፈ አይ​ደ​ለ​ምን? ነገር ግን በሸ​መ​ገለ ጊዜ እግ​ሮቹ ታመሙ። አሳም እንደ አባ​ቶቹ አን​ቀ​ላፋ፤ በአ​ባ​ቱም በዳ​ዊት ከተማ ከአ​ባ​ቶቹ ጋር ተቀ​በረ። ልጁም ኢዮ​ሣ​ፍጥ በፋ​ን​ታው ነገሠ።

1 ነገሥት 15:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ነገሠ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። እርሱም አባቱ ከርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም። ነገር ግን ከርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው። ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም። አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር። ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር። አብያም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በርሱ ፈንታ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ። የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ። አሳም ለአስጸያፊዋ የአሼራ ጣዖት ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። አሳ የማምለኪያ ኰረብቶችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር ፍጹም ነበር። እርሱና አባቱ የቀደሱትን ብር፣ ወርቅና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስገባ። አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር። የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት። አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በሹማምቱ እጅ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሃዳድ ላከ። “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑር። እነሆ፤ የብርና ወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋራ ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው። ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እርሱም ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ኪኔሬትን በሙሉ ድል አድርጎ ያዘ። ባኦስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን መገንባቱን አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ። ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ ሲሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ በእነርሱም ንጉሡ አሳ የብንያምን ጌባዕና ምጽጳን ሠራበት። በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ጀግንነቱ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹን ታመመ። አሳ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በርሱ ፈንታ ነገሠ።

1 ነገሥት 15:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለችው የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኀጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም። ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤ ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና። በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ። የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ። በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በኻያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፤ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ። በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው። ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ። አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው። በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ። አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ “በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ፤” ብሎ ሰደደ። ቤንሀዳድም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ። ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ። ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ።

1 ነገሥት 15:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች፤ አቢያም፥ እንደ ታላቁ አያቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በመገኘት ፈንታ፥ አባቱ ሮብዓም ይፈጽመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራቱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም በሰላም እንዲጠብቅ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው፥ እግዚአብሔር ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሒታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረጉና ትእዛዙንም በብርቱ ጥንቃቄ በመጠበቁ ነው። በአቢያ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፥ በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦር ሳያቋርጥ ቀጠለ፤ አቢያ ያደረገውም ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ። ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፤ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ፥ የቀድሞ አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ንጉሥ አሳ በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የቤተ ጣዖትን አመንዝራዎችን ሁሉ ከሀገሪቱ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖቶችንም ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ። አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው። አሳ በኰረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ ባያስወግድም እንኳ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ኖረ። አባቱ ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ ከወርቅና ከብር አሠርቶ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ያደረጋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ። የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ በማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። ባዕሻ ይሁዳን በመውረር ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፤ ይህንንም ያደረገው ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባና ከዚያም ማንም እንዳይወጣ ለመከልከል ነው። በዚህም ምክንያት ንጉሥ አሳ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ በማውጣት በባለሟሎቹ እጅ፥ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የጣብሪሞን ልጅ፥ የሔዝዮን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዐይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላክኹልህ ገጸ በረከት ነው፤ እንግዲህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላክ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ እነርሱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘውን አገርና የንፍታሌምን ግዛት ሁሉ ያዙ። ንጉሥ ባዕሻ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ራማን የመመሸጉ ሥራ እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ፥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ ምጽጳንና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት። ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ የጀግንነት ሥራውና የመሸጋቸውም ከተሞች ጭምር በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ግን ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር። እርሱም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ።

1 ነገሥት 15:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አቢያም፥ እንደ ታላቁ አያቱ እንደ ዳዊት በጌታ ዘንድ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በመገኘት ፈንታ፥ አባቱ ሮብዓም ይፈጽመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራቱን ቀጠለ። ይሁን እንጂ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም በሰላም እንዲጠብቅ ጌታ አምላኩ ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው። ጌታ ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሒታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር ጌታን ደስ የሚያሰኝ ነገር በማድረጉና ትእዛዙንም በብርቱ ጥንቃቄ በመጠበቁ ነው። በአቢያ ዘመነ መንግሥት ሁሉ፥ በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦርነት ሳያቋርጥ ቀጠለ። አቢያ ያደረገውም ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ በኋላ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ። ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፤ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ፥ የቀድሞ አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ ጌታን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ንጉሥ አሳ በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የቤተ ጣዖትን አመንዝራዎችን ሁሉ ከሀገሪቱ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖቶችንም ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ። አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው። አሳ በኰረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ ባያስወግድም እንኳ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ለጌታ ታማኝ ሆኖ ኖረ። አባቱ ለጌታ የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ ከወርቅና ከብር አሠርቶ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ያደረጋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ። የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ በማያቋርጥ የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። ባዕሻ ይሁዳን በመውረር ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፤ ይህንንም ያደረገው ወደ ይሁዳ ማንም እንዳይገባና ከዚያም ማንም እንዳይወጣ ለመከልከል ነው። በዚህም ምክንያት ንጉሥ አሳ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ በማውጣት በባለሟሎቹ እጅ፥ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የጣብሪሞን ልጅ፥ የሔዝዮን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፤ ከስጦታውም ጋር እንዲህ የሚል መልእክት ነበረ፤ “የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዓይነት በመካከላችን የስምምነት ውል እናድርግ፤ ይህም ብርና ወርቅ ለአንተ የላክኹልህ ገጸ በረከት ነው፤ እንግዲህ የእስራኤል ንጉሥ ባዕሻ ወታደሮቹን ከግዛቴ ያስወጣ ዘንድ እንድትረዳኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አሁን እንድታፈርሰው እለምንሃለሁ።” ንጉሥ ቤንሀዳድም አሳ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላክ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፤ እነርሱም ዒዮን፥ ዳን፥ አቤልቤትማዕካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘውን አገርና የንፍታሌምን ግዛት ሁሉ ያዙ። ንጉሥ ባዕሻ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ራማን የመመሸጉ ሥራ እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ፥ ባዕሻ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ ምጽጳንና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት። ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ የጀግንነት ሥራውና የመሸጋቸውም ከተሞች ጭምር በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ግን ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር። እርሱም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ።