1 ነገሥት 10:1-5
1 ነገሥት 10:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፥ የእግዚአብሔርንም ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ ነገረችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ያልተረጐመላትና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ የሰሎሞንንም የማዕዱን መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥርዐት፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ተደነቀች።
1 ነገሥት 10:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ዝና እና ከእግዚአብሔር ስም ጋር ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች። ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቶ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ዕንቈች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ንጉሡ አቅቶት የቀረ አንዳች ጥያቄ አልነበረም። ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አሳላፊዎቹን ከነደንብ ልብሳቸው፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ስታይ እጅግ ተደነቀች።
1 ነገሥት 10:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም።
1 ነገሥት 10:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫነ ሽቶ፥ የከበረ ዕንቊና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በሐሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት፤ እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጒምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዐይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች፤ በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዐይነት፥ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የደንብ ልብሳቸውንም ዐይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር።
1 ነገሥት 10:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫኑ ሽቶ፥ የከበረ ዕንቁና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በሐሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጉምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዓይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች። በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዓይነት፥ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የደንብ ልብሳቸውንም ዓይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር።