1 ቆሮንቶስ 12:21-26
1 ቆሮንቶስ 12:21-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዐይን እጅን፥ “አልፈልግሽም” ልትላት አትችልም፤ ራስም፥ “እግሮችን አልፈልጋችሁም” ልትላቸው አትችልም። ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉህ ናቸው። ከአካልም ክፍሎች የተናቁ ለሚመስሉን ክብርን እንጨምርላቸዋለን፤ ለምናፍርባቸውም የአካል ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል። ለከበረው የአካላችን ክፍል ክብርን አንሻለትም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውነታችንን አስማምቶታል፤ ይልቁንም ታናሹን የአካል ክፍል አክብሮታል። የአካላችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዳይለያዩ፥ አካላችን ሳይነጣጠል በክብር እንዲተካከል አስማማው። አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:21-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዐይን እጅን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ብልቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የተናቁ ለሚመስሉን ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ደግሞም የምናፍርባቸውን ብልቶች ይበልጥ እንንከባከባቸዋለን፤ የማናፍርባቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጐድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቷቸዋል፤ ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። አንድ ብልት ቢሠቃይ፣ ብልቶች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር፣ ሌሎቹም ብልቶች አብረው ደስ ይላቸዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:21-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዐይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ እንዲያውም በጣም ደካሞች መስለው የሚታዩ የአካል ክፍሎች ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው። አነስተኛ ክብር ያላቸው መስለው ለሚታዩን የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው ለሚታዩን የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ ክብር ሰጥተን እንጠነቀቅላቸዋለን፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካል ክፍሎች ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አገጣጥሞአል። ይህንንም ያደረገው በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንዱ የአካል ክፍል ሲሠቃይ ሌሎችም የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲከበር ሌሎቹም የሰውነት ክፍሎች አብረው ከእርሱ ጋር ይደሰታሉ።
1 ቆሮንቶስ 12:21-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዐይን እጅን “አታስፈልገኝም፤” ልትለው አትችልም፤ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን “አታስፈልጉኝም፤” ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ክፍሎች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉንን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፤ በምናፍርባቸውም የአካላችን ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካላችን ክፍሎች ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አስማምቷል። ይህም በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንድም አካል ቢሠቃይ የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ፤ አንድ አካልም ቢከበር የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።