1 ቆሮንቶስ 12:1-11
1 ቆሮንቶስ 12:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታም ታውቁ ዘንድ እንጂ አላዋቆች ልትሆኑ አንወድድም። ቀድሞም እናንተ አሕዛብ በነበራችሁ ጊዜ ዲዳዎች ጣዖታትን ታመልኩ እንደ ነበር፥ ጣዖትም በማምለክ ረክሳችሁ እንደ ነበር፥ ወደ ወሰዱአችሁም ትሄዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። ስለዚህም ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር፥ “ኢየሱስ ውጉዝ ነው” የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል አንድስ እንኳን እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው። ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ። ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፤ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ። ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። በዚህም ሁሉ ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይረዳል፤ ለሁሉም እንደ ወደደ ያድላቸዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ አሁን ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ይህን እንድታውቁ እፈልጋለሁ። አረማውያን በነበራችሁበት ጊዜ ወዲያና ወዲህ በመነዳት ድዳ ወደ ሆኑ ጣዖታት እንደ ተወሰዳችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ የሚናገር፣ “ኢየሱስ የተረገመ ነው” የሚል የለም፤ እንደዚሁም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር፣ ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚል እንደሌለ እነግራችኋለሁ። ስጦታዎች ልዩ ልዩ ሲሆኑ፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ጌታ ግን አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ሁሉን በሁሉ የሚሠራው ግን ያው አንዱ እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። ለአንዱ በመንፈስ የጥበብን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የዕውቀትን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለአንዱ በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታዎች ይሰጠዋል፤ ለአንዱ ታምራትን የማድረግ፣ ለሌላው ትንቢትን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ መናፍስትን የመለየት፣ ለአንዱ በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ በልዩ ልዩ ልሳን የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ ይሰጠዋል። እነዚህ ሁሉ የዚያው የአንዱ መንፈስ ስጦታዎች ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ ይሰጠዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አሕዛብ ሳላችሁ በማናቸውም ጊዜ እንደምትመሩ ድምፅ ወደሌላቸው ወደ ጣዖታት እንደ ተወሰዳችሁ ታውቃላችሁ። ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር፦ ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር፦ ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።
1 ቆሮንቶስ 12:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞቼ ሆይ! አሁን ደግሞ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንድታውቁ እፈልጋለሁ። አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ በማታውቁት ነገር ተመርታችሁ መናገር ወደማይችሉ ጣዖቶች ትወሰዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ኢየሱስን የሚረግም ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው!” የሚል ማንም እንደሌለ እነግራችኋለሁ። ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ የሥራ ዐይነቶችም አሉ፤ ነገር ግን ሁሉንም በሁሉ የሚያከናውን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ መንፈስ ቅዱስን የመግለጥ ስጦታ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። መንፈስ ቅዱስ ለአንዱ ሰው በጥበብ የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ሰው ደግሞ ያው መንፈስ በዕውቀት የመናገርን ችሎታ ይሰጠዋል፤ ያው አንዱ መንፈስ ለአንዱ እምነትን ይሰጠዋል፤ ለሌላውም የመፈወስ ስጦታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው የትንቢትን ቃል የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ወይም ከርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ለይቶ የማወቅ ችሎታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታን ይሰጠዋል፤ ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል።
1 ቆሮንቶስ 12:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ! አላዋቂ እንድትሆኑ አልፈልግም። አሕዛብ በነበራችሁበት ጊዜ በማታውቁት ነገር ተመርታችሁ መናገር ወደማይችሉ ጣዖቶች ትወሰዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር “ኢየሱስ የተረገመ ነው፤” የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው፤” ሊል ማንም እንደማይችል አስታውቃችኋለሁ። ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም አሉ፤ አሠራሮችም ልዩ ልዩ አሉ፤ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ ግን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ የመንፈስን መገለጥ የሚሰጠው ለጥቅም ነው። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላውም ያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ በዚያው መንፈስ ለአንዱ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው የመፈወስ ስጦታን በዚያው አንድ መንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ተአምራትን የማድረግ ኃይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱ መናፍስትን መለየት፥ ለሌላው በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለሌላውም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን አንዱና ያው መንፈስ ያደርጋል፤ እንደፈቃዱም ለእያንዳንዱ ሰው ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።