1 ቆሮንቶስ 1:17-25
1 ቆሮንቶስ 1:17-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክርስቶስ ወንጌልን ለመስበክ እንጂ ለማጥመቅ አልላከኝምና፥ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም። የመስቀሉ ነገር በሚጠፉ ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፥ ለምንድነው ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “እኔ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የመካሪዎችንም ምክር እንቃለሁ።” እንግዲህ ጥበበኛ ማን ነው? ጸሓፊስ ማን ነው? ይህን ዓለምስ የሚመረምረው ማን ነው? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ስንፍና አላደረገውምን? ሰዎች በጥበባቸው በማያውቁት በእግዚአብሔር ጥበብ ስንፍና በሚመስላቸው ትምህርት ያመኑትን ሊያድናቸው እግዚአብሔር ወድዶአልና። አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ስንፍና ነው። ለእኛ ለዳንነው ግን ከአይሁድ፥ ከአረሚም ብንሆን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። የእግዚአብሔር ስንፍና ከሰው ይልቅ ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።
1 ቆሮንቶስ 1:17-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ክርስቶስ የላከኝ ወንጌልን እንድሰብክ እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፣ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም። የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የዐዋቂዎችንም ዕውቀት ከንቱ አደርጋለሁ።” ጠቢብ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገምን? ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗል። መቼም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው። እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል።
1 ቆሮንቶስ 1:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።
1 ቆሮንቶስ 1:17-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ክርስቶስ የላከኝ የወንጌልን ቃል እንዳስተምር ነው እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር የወንጌልን ቃል የማስተምረው ከሰው ጥበብ በተገኘ ንግግር አይደለም። የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሰዎች እንደ ሞኝነት ይቈጠራል፤ ለምንድን ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ዕውቀት አስወግዳለሁ” ተብሎ ተጽፎአል። ታዲያ፥ ጥበበኛ የት አለ? የሕግ ምሁርስ የት አለ? ተመራማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አድርጎት የለምን? የዚህ ዓለም ሰዎች በገዛ ጥበባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ እንዳይችሉ እግዚአብሔር በጥበቡ ዘጋባቸው፤ ነገር ግን እንደ ሞኝነት በሚቈጠረው እኛ በምናስተምረው ወንጌል የሚያምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል። መቼም አይሁድ ተአምር ማየትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎች ደግሞ ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን ክርስቶስ ስለ እኛ መሰቀሉን እናስተምራለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናከያ ነው፤ ለግሪክ ሰዎች ደግሞ ሞኝነት ነው። ለተጠሩት ግን ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። የእግዚአብሔር ሞኝነት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነገር ከሰው ጥበብ ይበልጣል፤ የእግዚአብሔር ደካማነት ነው ተብሎ የሚታሰበውም ነገር ከሰው ኀይል ይበልጣል።
1 ቆሮንቶስ 1:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንጌልን ላስተምር እንጂ ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር፥ በቃል ጥበብም አይደለም። የመስቀሉ መልዕክት ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ፤” ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚህ ዘመን ተከራካሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በምንሰብከው ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ ግሪኮችም ጥበብን ይሻሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፤ ለተጠሩት ግን፥ ለአይሁዶች ሆነ ለግሪኮችም፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፤ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።