ትንቢተ ሶፎንያስ 2
2
1-2እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፥ ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ትኵሳት ሳይመጣባችሁ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም። 3እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፥ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።
4ጋዛ ትበረበራለች፥ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፥ አዛጦንንም በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዱአታል፥ አቃሮንም ትነቀላለች። 5በባሕር ዳር ለሚኖሩ ለከሊታውያን ሕዝብ ወዮላቸው! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የእግዚአብሔር ቃል በአንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብህም ሰው እንዳይኖር አጠፋሃለሁ። 6ቀርጤስም የእረኞች መኖሪያና የመንጎች በረት ይሆናል። 7የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ቅሬታ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፥ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳልና በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ።
8በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፥ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ። 9ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፥ የሳማ ስፍራና የጨው ጕድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፥ የሕዝቤም ቅሬታ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል። 10በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ እየታበዩም ተናግረዋልና ይህ ስለ ትዕቢታቸው ያገኛቸዋል። 11እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፥ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
12እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ። 13እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፥ ነነዌንም ባድማ፥ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል። 14መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጥዋ ይመሰጋሉ፥ ይብራና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፥ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል፥ የዝግባም እንጨት ሥራ ይገለጣልና በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል። 15ተዘልላ የተቀመጠች፥ በልብዋም፦ እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ያለች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፥ አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ እንዴት ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፍዋጫል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሶፎንያስ 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ