የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 11

11
1ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ። 2የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ ከበርቴዎችም ጠፍተዋልና ዋይ በል፥ እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና ዋይ በሉ። 3የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸው ድምፅ ተሰምቶአል፥ የዮርዳኖስ ትዕቢት ተዋርዶአልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ተሰምቶአል።
4አምላኬ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል፦ ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ። 5የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ ራሳቸውንም እንደ በደለኞች አድርገው አይቈጥሩም፥ የሸጡአቸውም፦ ባለ ጠጋ ሆነዋልና እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ፥ እረኞቻቸውም አይራሩላቸውም። 6ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ በባልንጀራውና በንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ ምድሪቱም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላድናቸውም።
7እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፥ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፥ መንጋውንም ጠበቅሁ። 8በአንድ ወርም ሦስቱን እረኞች አጠፋሁ፥ ነፍሴም ተሰቀቀቻቸው፥ ነፍሳቸውም ደግሞ እኔን ጠላች። 9እኔም፦ እናንተን አልጠብቅም፥ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፥ የቀረውም እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሥጋ ይብላ አልሁ። 10እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፈርስ ዘንድ ውበት የተባለችውን በትሬን ወስጄ ቈረጥሁ። 11በዚያም ቀን ተሰበረች፥ እንዲሁም እኔን የተመለከቱ የመንጋው ችግረኞች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አወቁ። 12እኔም፦ ደስ ብሎአችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፥ ያለዚያ ግን ተውት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። 13እግዚአብሔርም፦ የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት። 14በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት እሰብር ዘንድ ማሰሪያ የተባለቸውን ሁለተኛይቱን በትሬን ቈረጥሁ።
15እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ። 16እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፥ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፥ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል። 17መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፥ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽማ ትጨልማለች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ