የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዘካርያስ 10

10
1በኋለኛው ዝናብ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዝናቡን ለምኑ፥ እግዚአብሔር መብረቅ ያደርጋል፥ እርሱም የበልግ ዝናብን ለእያንዳንዱም በሜዳ ውስጥ ሣርን ይሰጣል። 2ተራፊም ከንቱነትን ተናግረዋልና፥ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፥ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል፥ በከንቱም ያጽናናሉ፥ እረኛም የላቸውምና እንደ በጎች ተቅበዝብዘዋል ተጨንቀውማል።
3ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዶአል፥ አውራ ፍየሎችንም እቀጣለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የይሁዳን ቤት መንጋውን ጐብኝቶአል፥ በሰልፍም ውስጥ እንዳለ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል። 4ከእርሱ ዘንድ የማዕዘኑ ድንጋይ፥ ከእርሱም ዘንድ ችንካሩ፥ ከእርሱም ዘንድ የሰልፍ ቀስት፥ ከእርሱም ዘንድ አስገባሪው ሁሉ በአንድ ላይ ይመጣሉ። 5በሰልፍም ጊዜ ጠላቶቻቸውን በመንገድ ጭቃ ውስጥ እንደሚረግጡ ኃያላን ይሆናሉ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነውና ይዋጋሉ፥ ፈረሰኞችም ያፍራሉ። 6ወድጃቸዋለሁና የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፥ የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ፥ አደላድላቸዋለሁም፥ እመልሳቸዋለሁ፥ እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፥ እኔም እሰማቸዋለሁና እንዳልጣልኋቸው ይሆናሉ። 7የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል፥ ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በእግዚአብሔር ሐሤት ያደርጋል።
8ተቤዥቼአቸዋለሁና በፉጨት ጠርቼ እሰበስባቸዋለሁ፥ ቀድሞም በዝተው እንደ ነበሩ ይበዛሉ። 9በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳ በሩቅ አገር ሳሉ ያስቡኛል፥ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይኖራሉ፥ ይመለሱማል። 10ከግብጽም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ ምድር አመጣቸዋለሁ፥ የሚበቃም ቦታ አይገኝላቸውም። 11እርሱም በጭንቅ ባሕር ያልፋል፥ የባሕርንም ሞገድ ይመታል፥ የወንዙም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል፥ የአሦርም ትዕቢት ይዋረዳል፥ የግብጽም በትረ መንግሥት ይርቃል። 12በአምላካቸው በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፥ በስሙም ይመካሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ