መጽሐፈ ሩት 1
1
አቤሜሌክና ቤተሰቡ ወደ ሞዓብ እንደተሰደዱ
1እንዲህም ሆነ፤ መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ሊቀመጥ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ። 2የሰውዮውም ስም አቤሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፤ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ በዚያም ተቀመጡ። 3የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ እርስዋና ሁለቱ ልጆችዋ ቀሩ። 4እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፤ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ። 5መሐሎንና ኬሌዎንም ሁለቱ ሞቱ፤ ሴቲቱም ከሁለቱ ልጆችዋና ከባልዋ ተለይታ ቀረች።
የኑኃሚን ከሩት ጋር ወደ ቤተልሔም መመለስ
6እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች። 7እርስዋም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፤ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ በመንገድ ሄዱ። 8ኑኃሚንም ምራቶችዋን “ሂዱ፤ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፤ በእኔና በሞቱት እንዳደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ቸርነት ያድርግላችሁ። 9እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ፤” አለቻቸው። ሳመቻቸውም፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ። 10እነርሱም “ከእንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን፤” አሉአት። 11ኑኃሚንም አለች “ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን? 12ልጆቼ ሆይ! ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ 13እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ! እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።” 14ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት። 15ኑኃሚንም “እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ፤” አለቻት። 16ሩትም “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዘሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ 17በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፤ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ እንዲሁም ይጨምርብኝ፤” አለች። 18ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች።
19ሁለቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” እያሉ ተንጫጩ። 20እርስዋም “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ። 21በሙላት ወጣሁ፤ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ?” አለቻቸው። 22ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሩት 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ