የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 9

9
1ከግብፅም ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤ 3በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት። 4ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው። 5በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። 6በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ። 7እነዚያም ሰዎች፦ በሞተ ሰው ሬሳ ረክሰናል፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን? አሉት። 8ሙሴም፦ እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ቈዩ አላቸው። 9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው በሬሳ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ። 11በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 12ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት። 13ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል። 14በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያደርግ ዘንድ ቢወድድ፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓት እንደ ፍርዱም እንዲሁ ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ሥርዓት ይሁንላችሁ። 15ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር። 16እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር። 17ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። 18በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። 19ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር። 20አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። 21አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 22ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 23በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ