ኦሪት ዘኊልቊ 32:20-42

ኦሪት ዘኊልቊ 32:20-42 አማ54

ሙሴም አላቸው፦ ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥ እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ። ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ። የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት፦ እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን። ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። ሙሴም፦ የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው። የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው፦ እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት። ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው። የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥ ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ ቂርያትይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ። የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው። ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።