ኦሪት ዘኊልቊ 2
2
1እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ 2የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን አፋዛዥ ዙሪያ ይስፈሩ። 3በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳ ሰፈር ዓላማ ሰዎች ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 4ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 5በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ። 6ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 7በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ። 8ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 9ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ። 10በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ። 11ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 12በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ። 13ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 14በእነርሱም አጠገብ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ። 15ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ። 16ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ አምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ። 17ከዚያም በኋላ የመገናኛው ድንኳን በሰፈሮቹም መካከል የሌዋውያን ሰፈር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው ሰው ሁሉ በየስፍራው በየዓላማውም ይጓዛሉ። 18በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ። 19ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 20በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ይሆናል፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ። 21ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 22በእነርሱም አጠገብ የብንያም ነገድ ይሆናል፤ የብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ። 23ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 24ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ። 25በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ። 26ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 27በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ። 28ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 29በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ይሆናል፤ የንፍታሌምምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ። 30ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 31ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ አምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ። 32ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 33ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 34የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ተጓዙ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ