የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 8:9-18

መጽሐፈ ነህምያ 8:9-18 አማ54

ሐቴርሰታ ነህምያም ጸሐፊውም ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፥ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ አሉአቸው፥ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። እርሱም፦ ሂዱ፥ የሰባውንም ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፥ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፥ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ አላቸው። ሌዋውያንም፦ ቀኑ የተቀደሰ ነውና ዝም በሉ፥ አትዘኑም ብለው ሕዝቡን ሁሉ ጸጥ ያደርጉ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ። በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች ካህናቱም ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጉምላቸው ዘንድ ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም፦ ወደ ተራራ ሂዱ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ የባርሰነትም የዘንባባም የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፥ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ ብለው ይናገሩ ያውጁም ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባዩ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠራ። ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፥ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፥ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጉ የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ።