ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። የክሱ ጽሕፈትም፦ የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። መጽሐፍም፦ ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ፦ ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር።
የማርቆስ ወንጌል 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 15:16-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos