የማርቆስ ወንጌል 14:22-31

የማርቆስ ወንጌል 14:22-31 አማ54

ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ኢየሱስም፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም፦ ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ፦ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።