ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስ፦ እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ጴጥሮስ፦ ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፦ እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና፦ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ።
የማቴዎስ ወንጌል 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 26:26-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች