በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፦ ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። እርሱም፦ ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። እጅግም አዝነው እያንዳንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስ፦ እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ጴጥሮስ፦ ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
የማቴዎስ ወንጌል 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 26:14-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች