የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 6:17-26

የሉቃስ ወንጌል 6:17-26 አማ54

ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።