በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ፦ በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ፦ ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም። በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፦ ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ። በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።
የሉቃስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 6:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች