ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። ጠይቀውም፦ መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ፦ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም፦ የቄሣር ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ። ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥ እንዲህ ሲሉ፦ መምህር ሆይ፥ ሙሴ፦ ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም አገባት፥ ሦስተኛውም፥ እንዲሁም ሰባቱ ደግሞ ልጅ ሳይተዉ ሞቱ። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች? ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥ ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው፦ መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት። ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም። እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ይላል። እንግዲህ ዳዊት፦ ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን፦ ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።
የሉቃስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 20:20-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች