የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 1:1-80

የሉቃስ ወንጌል 1:1-80 አማ54

የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን፦ እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ። የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። ማርያምም እንዲህ አለች፦ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል። ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። እናቱ ግን መልሳ፦ አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። እነርሱም፦ ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። ብራናም ለምኖ፦ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፦ እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦ የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።