ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:37-66

ሰቈቃወ ኤርምያስ 3:37-66 አማ54

ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው? ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን? ሕያው ሰው የሚያጉረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጕረመርም ስለ ምንድር ነው? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ። በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም። ሳምኬት። በቍጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፥ ገደልኸን፥ አልራራህም። ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ። በአሕዛብ መካከል ጕድፍና ውዳቂ አደረግኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን። ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፥ እኔም፦ ጠፋሁ ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። ድምፄን ሰማህ፥ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ቀርበህ፦ አትፍራ አልህ። ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፥ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ። የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ። አቤቱ፥ በቍጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።