መጽሐፈ ኢያሱ 24
24
1ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 2ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፥ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። 3አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፥ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። 4ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፥ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፥ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ። 5ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፥ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው። 6አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፥ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። 7ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፥ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፥ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። 8እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፥ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። 9የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፥ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። 10እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፥ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። 11ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፥ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። 12በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። 13ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፥ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።
14አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፥ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። 15እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።
16ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፦ እግዚአብሔርን ትተን ሌሎችን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፥ 17እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። 18እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱ የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፥ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን።
19ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፥ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። 20እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። 21ሕዝቡም ኢያሱን፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት። 22ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ አላቸው፥ እነርሱም፦ ምስክሮች ነን አሉ። 23እርሱም፦ አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ አላቸው። 24ሕዝቡም ኢያሱን፦ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን አሉት።
25በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። 26ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፥ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። 27ኢያሱም ለሕዝቡ፦ እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፥ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል አላቸው። 28ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ።
29እንዲህም ሆነ፥ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። 30በተራራማው በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። 31ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ።
32የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በግ በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፥ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። 33የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፥ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 24: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ