የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 11

11
1እንዲህም ሆነ፥ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥ 2በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ 3በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። 4እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞና ሠረገሎች ጋር ወጡ፥ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ። 5እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ።
6እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፥ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው። 7ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም። 8እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፥ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። 9ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፥ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።
10በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፥ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። 11በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፥ አሶርንም በእሳት አቃጠላት። 12የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። 13እስራኤልም በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም፥ ነገር ግን እስራኤል አሶርን ብቻ አቃጠሉአት። 14የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፥ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። 15እግዚአብሔርም ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፥ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም።
16ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ 17እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በአልጋድ ድረስ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። 18ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። 19በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፥ ሁሉን በሰልፍ ያዙ። 20እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ ሞገስንም እንዳያገኙ ፈጽመውም እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ።
21በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፥ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። 22በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። 23እግዚአብሔርም ለሙሴ እንደ ነገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፥ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸውና እንደ ነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፥ ምድሪቱም ከሰልፍ ዐረፈች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ