መጽሐፈ ኢዮብ 4
4
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ፦
2አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀይማለህን?
ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው?
3እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥
የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥
አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።
5አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፥
ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ።
6አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥
የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን?
7እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው?
ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?
8እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥
መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።
9በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥
በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።
10የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥
የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ።
11አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥
የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ።
12ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥
ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች።
13በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥
የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥
14አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ
ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ።
15መንፈስም በፊቴ አለፈ፥
የሥጋዬ ጠጕር ቆመ።
16እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥
ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፥
የዝምታ ድምፅ ሰማሁ፦
17በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥
ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን?
18እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፥
መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፥
19ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥
መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥
ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?
20በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፥
ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ።
21ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን?
አለጥበብም ይሞታሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ