መጽሐፈ ኢዮብ 34
34
1ኤሊሁም ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፥
እናንተም አዋቂዎች፥ ወደ እኔ አድምጡ።
3ትናጋ መብልን እንደሚቀምስ፥
ጆሮ ቃልን ትለያለችና።
4ቅን የሆነውን ነገር እንምረጥ፥
መልካሙንም ነገር በመካከላችን እንወቅ።
5ኢዮብ፦ እኔ ጻድቅ ነኝ፥
እግዚአብሔር ግን ፍርዴን አስወገደ፥
6ምንም እውነተኛ ብሆን እንደ ውሸተኛ ተቈጠርሁ፥
ምንም ባልበድል ቍስሌ የማይፈወስ ነው ብሎአል።
7-9ኢዮብም፦ በእግዚአብሔር መደሰት
ለሰው ምንም አይጠቅምም ብሎአልና
ከበደለኞች ጋር የሚተባበር፥
ክፉ ከሚያደርጉስ ጋር የሚሄድ፥
መሳለቅን እንደ ውኃ የሚጠጣት
እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?
10ስለዚህ እናንተ አእምሮ ያላችሁ ሰዎች፥ ስሙኝ፥
ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር፥
በደልንም ይሠራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።
11ለሰው ሥራውን ይመልስለታል፥
ሰውም እንደ መንገዱ ያገኝ ዘንድ ያደርጋል።
12በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥
ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።
13ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው?
ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው?
14እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥
መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥
15ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥
ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል።
16አስተዋይ ብትሆን ይህን ስማ፥
የንግግሬንም ቃል አድመጥ።
17በውኑ ጽድቅን የሚጠላ ይሠለጥናልን?
ጻድቅና ኃያል የሆነውስ በደለኛ ታደርገዋለህን?
18ማንም ሰው ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ፥
መኳንንቱንም፦ ክፉዎች ናችሁ ይላልን?
19እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና
በአለቆች ፊት አያደላም፥
ባለጠጋውንም ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም።
20እነርሱ በመንፈቀ ሌሊት በድንገት ይሞታሉ፥
ሕዝቡ ተንቀጥቅጦ ያልፋል፥
ኃያላንም ያለ እጅ ይነጠቃሉ።
21ዓይኖቹ በሰው መንገድ ላይ ናቸው፥
እርምጃውንም ሁሉ ያያል።
22ኃጢአትን የሚሠሩ ይሰወሩበት ዘንድ
ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም።
23ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመፈራረድ እንዲመጣ
ጊዜ አይወሰንለትም።
24ታላላቆችን ያለ ምርመራ ይሰባብራል፥
በእነርሱም ፋንታ ሌሎችን ያቆማል።
25ሥራቸውን ያውቃል፥
እንዲደቅቁም በሌሊት ይገለባብጣቸዋል።
26ሰዎች እያዩ እንደ ክፉዎች ይመታቸዋል፥
27-28የድሀውን ልቅሶ ወደ እርሱ ያደርሱ ዘንድ፥
እርሱም የችግረኛውን ድምፅ ይሰማ ዘንድ፥
እርሱን ከመከተል ፈቀቅ ብለዋልና፥
ከመንገዱም ሁሉ አንዱን አልተመለከቱምና።
29በሕዝብ ወይም በሰው ዘንድ ቢሆን፥
እርሱ ቢያሳርፍ የሚፈርድ ማን ነው?
ፊቱንስ ቢሰውር የሚያየው ማን ነው?
30ይህም ዝንጉ ሰው እንዳይነግሥ፥
ሕዝቡንም የሚያጠምድ እንዳይኖር ነው።
31እግዚአብሔርን፦ እኔ ሳልበድል ቅጣት ተቀበልሁ፥
32የማላየውን ነገር አንተ አስተምረኝ፥
ኃጢአትንም ሠርቼ እንደ ሆነ፥
ደግሜ አልሠራም የሚለው ማን ነው?
33በውኑ አንተ ጥለኸዋልና
ፍዳው አንተ እንደምትወድደው ይሆናልን?
አንተ ትመርጣለህ እንጂ እኔ አይደለሁም፥
ስለዚህ የምታውቀውን ተናገር።
34የሚሰሙኝ ጥበበኞች ሁሉ፥
አስተዋዮችም እንዲህ ይሉኛል፦
35ኢዮብ ያለ እውቀት ተናግሮአል፥
ቃሉም በአእምሮ አይደለችም።
36ኢዮብ እስከ ፍጻሜ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ!
እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና፥
37በኃጢአቱም ላይ ዓመፅን ጨምሮአልና፥
በእኛም መካከል በእጅ ያጨበጭባልና፥
ቃልንም በእግዚአብሔር ላይ ያበዛልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 34: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ