የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 24

24
1ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና
እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም?
2የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፥
መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ።
3የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፥
የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ።
4ድሆቹን ከመንገድ ያወጣሉ፥
የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ።
5እነሆ፥ በምድር በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥
መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፥
ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።
6እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፥
የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ።
7ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥
በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም።
8ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፥
መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ።
9ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ፥
ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ።
10ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፥
ተርበው ነዶዎችን ይሸከማሉ፥
11በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፥
ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ።
12ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፥
የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፥
እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም።
13እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፥
መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።
14ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፥
ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፥
በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።
15የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል፦
የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥
ፊቱንም ይሸፍናል።
16ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፥
በቀን ይሸሸጋሉ፥
ብርሃንም አያውቁም።
17የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፥
የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና።
18እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፥
እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፥
ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም።
19ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፥
እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች።
20ማኅፀን ትረሳዋለች፥
ትልም በደስታ ይጠባዋል፥
ዳግመኛም አይታሰብም፥
ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።
21የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፥
ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም።
22ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፥
እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።
23እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥
በዚያም ይታመናሉ፥
ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው።
24ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፥
ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፥
እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፥
እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ።
25እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥
ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ